ይሁዳ 1:1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፤ ለተጠሩት፣ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቁት፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስም ለተጠበቁት፥ ለተጠሩት፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና የያዕቆብ ወንድም ከሆነው ከይሁዳ፥ ለተጠራችሁት፥ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዳችሁት፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቃችሁት ሁሉ፥ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፦ |
ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን?” አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር።
እኔን የሚያገለግለኝ ካለ ይከተለኝ፤ የሚያገለግለኝ እኔ ባለሁበት በዚያ ይኖራልና፤ እኔን የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል።
የአስቆሮቱ ሰው ያይደለ ይሁዳም፥ “ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ያይደለ ለእኛ ራስህን ትገልጥ ዘንድ እንዳለህ የተናገርኸው ምንድን ነው?” አለው።
እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ የመረጣችሁኝ አይደለም፤ እንድትሄዱ፥ ፍሬም እንድታፈሩ፥ ፍሬአችሁም እንዲኖር፤ አብንም በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ሁሉን እንዲሰጣችሁ ሾምኋችሁ።
የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድስ እንኳ ቢሆን እንዳይጠፋ ነው፤ ነገር ግን እኔ በኋለኛዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ።
ወደ ማደሪያቸውም በደረሱ ጊዜ ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ ማቴዎስ፥ በርተሎሜዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ።
አሁንም ለእግዚአብሔርና ሊያንጻችሁ፥ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።
የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማስተማር ተለይቶ ከተጠራ ሐዋርያ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሚሆን ከጳውሎስ፥
እነርሱ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያይደለ ለሆዳቸው ይገዛሉና፤ በነገር ማታለልና በማለዛዘብም የብዙዎች የዋሃንን ልብ ያስታሉ፤
ዛሬ ግን ከኀጢአት ነጻ ወጣችሁ፤ ራሳችሁንም ለጽድቅ አስገዛችሁ፤ ለቅድስናም ፍሬን አፈራችሁ፤ ፍጻሜው ግን የዘለዓለም ሕይወት ነው።
በቆሮንቶስ ሀገር ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለከበሩና ቅዱሳን ለተባሉ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ለሚጠሩ ሁሉ፥
እንግዲህ እናንተ እንዲህ ስትሆኑ እነማን ናችሁ? ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋልም።
የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።
ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፤ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ፥ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤
አሁንም ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞቻችን ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፥ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችሁማል፤ ያበረታችሁማል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።