Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ጢሞቴዎስ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)

1 በእግዚአብሔር ፊት፥ በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤

2 ቃሉን ስበክ፤ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፤ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ ዝለፍና ገሥጽ፤ ምከርም።

3 ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።


ጳውሎስ የጽድቅን አክሊል ለመቀዳጀት ተስፋ እንዳደረገ

4 እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።

5 አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤ አገልግሎትህን ፈጽም።

6 በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል።

7 መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፤ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤

8 ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።


ስለ ግል ጉዳዮች

9 በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤

10 ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል፤ ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል።

11 ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ፤ ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው።

12 ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ላክሁት።

13 ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ።

14 የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ እጅግ ከፋብኝ፤ ጌታ እንደ ሥራው ይመልስለታል።

15 አንተም ደግሞ ከእርሱ ተጠበቅ፤ የምንናገረውን እጅግ ተቃውሞአልና።

16 በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፤ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤

17 ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ።

18 ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።


የመጨረሻ ሰላምታ

19 ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ።

20 ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፤ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በሚሊጢን ተውሁት።

21 ከክረምት በፊት እንድትመጣ ትጋ። ኤውግሎስና ጱዴስ ሊኖስም ቅላውዲያም ወንድሞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

22 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos