ሐዋርያት ሥራ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያደርገውና ሊያስተምረው የጀመረውን ሥራ ሁሉ አስቀድሜ በመጽሐፍ ጽፌልሃለሁ። 2 በመንፈስ ቅዱስ የመረጣቸው ሐዋርያትን አዝዞ እስከ ዐረገባት ቀን ድረስ ያለውን ጽፌልሃለሁ። 3 ሕማማትን ከተቀበለ በኋላ ብዙ ተአምራት በማሳየት አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየነገራቸውና እያስተማራቸው ሕያው ሆኖ ራሱንገለጠላቸው። ስለ ተስፋና ስለ ጥምቀት። 4 ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ፥ “ከእኔ የሰማችሁትን የአብን ተስፋ ጠብቁ” ብሎ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው። 5 “ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን እስከ ቅርብ ቀን ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” አላቸው። 6 እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ፥ “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት። 7 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም። 8 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፥ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮች ትሆኑኛላችሁ።” ስለ ዕርገት 9 ይህንም እየነገራቸው ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ተቀበለችው፤ እነርሱም ወደ እርሱ እያዩ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ከዐይናቸውም ተሰወረ። 10 እነርሱም ወደ ሰማይ አተኵረው ሲመለከቱ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች ነጫጭ ልብስ ለብሰው በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው። 11 እነርሱም፥ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየአያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፥ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል” አሏቸው። 12 ከዚህም በኋላ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ለኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። 13 ወደ ማደሪያቸውም በደረሱ ጊዜ ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ ማቴዎስ፥ በርተሎሜዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ። 14 እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከጌታችን ከኢየሱስ እናት ከማርያም፥ ከወንድሞቹም ጋር በአንድነት ለጸሎት ይተጉ ነበር። ስለ ሐዋርያዊት ምርጫ 15 ያንጊዜም ጴጥሮስ ተነሣና በወንድሞቹ መካከል ቆመ፤ መቶ ሃያ ያህል ሰዎችም በዚያ ሳሉ እንዲህ አላቸው። 16 “እናንተ ሰዎች ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ ጌታችን ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባል። 17 እርሱም ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበር፤ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበር። 18 ከዚህም በኋላ ይህ ሰው በዐመፅ ዋጋዉ መሬት ገዛ፤ በምድር ላይም በግንባሩ ወደቀና ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ። 19 በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ዜናዉ ተሰማ፤ ያም መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ ይኸውም የደም መሬት ማለት ነው። 20 በመዝሙር መጽሐፍ ‘መኖሪያዉ ምድረ በዳ ትሁን፤ በውስጧም የሚኖር አይኑር፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ’ ተብሎ ተጽፎአልና። 21 እንግዲህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ 22 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤዉ ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል።” 23 ኢዮስጦስ የሚሉትን በርናባስ የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን ሰዎች አቆሙ። 24 እንዲህም ብለው ጸለዩ፥ “አቤቱ፥ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ፥ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥኸውን አንዱን ግለጥ። 25 ይሁዳ ወደ ሀገሩ ይሄድ ዘንድ የተዋትን ይህቺን የአገልግሎትና የሐዋርያነትን ቦታ የሚቀበላትን ግለጥ።” 26 ዕጣም አጣጣሏቸው፤ ዕጣዉም በማትያስ ላይ ወጣ፤ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋራም ተቈጠረ። |