ሐዋርያት ሥራ 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጳውሎስ ወደ ሮም በመርከብ ስለ መሔዱ 1 ከዚህም በኋላ ፊስጦስ ወደ ቄሣር ወደ ኢጣልያ በመርከብ እንሄድ ዘንድ ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስ ከሌሎች እስረኞች ጋር አብሮ የአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚባል የመቶ አለቃ ተሰጠ። 2 በተነሣንም ጊዜ ወደ እስያ በምትሄድ በአድራማጢስ መርከብ ተሳፈርን፤ የተሰሎንቄ ሀገር ሰው የሚሆን መቄዶንያዊው አርስጥሮኮስም አብሮን ሄደ። 3 በማግሥቱም ወደ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ አዘነለት፤ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና በእነርሱ ዘንድ እንዲያርፍም ፈቀደለት። 4 ከዚያም ወጥተን ነፋስ ፊት ለፊት ነበርና በቆጵሮስ በኩል ዐለፍን። 5 ወደ ኪልቅያና ወደ ጵንፍልያ ባሕርም ገብተን የሉቅያ ክፍል ወደምትሆነው ወደ ሙራ ሄድን። 6 በዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣልያ የምትሄድ የእስክንድርያን መርከብ አገኘ፤ ወደ እርስዋም አስገባን። 7 ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄድን፤ በጭንቅም ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ወደዚያም በቀጥታ ለመድረስ ነፋስ ቢከለክለን በቀርጤስ በኩል በሰልሙና ፊት ለፊት ዐለፍን። 8 ባጠገብዋም በጭንቅ ስናልፍ ላሲያ ለምትባለው ከተማ አቅራቢያ ወደ ሆነችው መልካም ወደብ ወደምትባለው ቦታ ደረስን። 9 በዚያም ብዙ ቀን ቈየን፤ የአይሁድም የጾም ወራት አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መከራቸው። 10 “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ስሙኝ፤ ጕዞአችን በብዙ ጭንቀትና በከባድ ጥፋት ላይ ሆኖ አያለሁ፤ ይህንም የምለው ጥፋቱ በራሳችንም ሕይወት እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ ስላልሆነ ነው።” 11 የመቶ አለቃው ግን ለመርከቡ ባለቤትና ለመሪው ይታዘዝ ነበር፤ የጳውሎስን ቃል ግን አይቀበልም ነበር። 12 ያም ወደብ ክረምቱን ሊከርሙበት የማይመች ነበር፤ ስለዚህም ብዙዎች ከዚያ ይወጡ ዘንድ ይቻላቸው እንደ ሆነ በቀኝ በኩል ወደ አለው ፊንቄ ወደሚባለው ወደ ሁለተኛው የቀርጤስ ወደብ ይደርሱ ዘንድ ወደዱ። ስለ ማዕበሉ ጽናት 13 ልከኛ የአዜብ ነፋስም ነፈሰ፤ እነርሱም እንደ ወደዱ የሚደርሱ መስሎአቸው ነበር፤ መልሕቁንም አነሡ፤ በቀርጤስም አጠገብ ሄዱ። 14 ከጥቂት ጊዜ በኋላም አውራቂስ የሚሉት ጽኑዕ ዓውሎ ነፋስ መጣ። 15 መርከባችንም ተመትታ ተነጠቀች፤ ቀዛፊዎችም በነፋሱ ፊት ለፊት መቆም አልተቻላቸውምና ተዉአት፤ ብቻዋንም ሄደች። 16 ከዚህም በኋላ ቄዳ ወደምትባል ደሴት እስክንገባ ድረስ ነፋሱ ነፈሰ፤ በጭንቅም ታንኳችንን ለመግታት ቻልን። 17 ከዚህ በኋላ ተጋግዘን በገመድ አጠናከርናት፤ ከዚህም ቀጥሎ ቀዛፊዎች ወደ ጥልቁ ባሕር እንዳይወድቁ በፈሩ ጊዜ ሸራውን አወረዱ፤እንዲሁም እንድንሄድ አደረግን። 18 በማግሥቱም ማዕበል ጸናብን፤ ከጭነቱም ወደ ባሕር ጣልን። 19 በሦስተኛውም ቀን በመርከብ ያለውን ሁሉ በእጃችን እያነሣን በባሕር ላይ ጣልን። 20 ብዙ ቀንም ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም ሳናይ ማዕበሉ ጸናብን፤ ለመዳንም ተስፋ ቈርጠን ነበር። ጳውሎስ በመርከብ ላሉት ሰዎች ስለ ተናገረው ነገር 21 ከእኛም መብል የበላ አልነበረም። ጳውሎስም ተነሥቶ በመካከል ቆመና እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ቀድሞ ቃሌን ሰምታችሁኝ ቢሆን ከቀርጤስም ባትወጡ ኖሮ ከዚህ ጕዳትና መከራ በዳናችሁ ነበር። 22 አሁንም እላችኋለሁ፤ መርከባችን እንጂ ከመካከላችን አንድ ሰው ስንኳ አይጠፋምና አትፍሩ። 23 እኔ ለእርሱ የምሆንና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና። 24 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ ከአንተም ጋር የሚሄዱትን ሁሉ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለአንተ ሰጥቶሃል።’ 25 አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ እንደ ነገረኝ እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና። 26 ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንደርሳለን።” 27 በዐሥራ አራተኛውም ቀን በመንፈቀ ሌሊት በአድርያ ባሕር ስንጓዝ ቀዛፊዎች ወደ የብሱ የደረሱ መሰላቸው። 28 መለኪያ ገመድ ጣሉ፤ በሰው ቁመትም ሃያ አገኙ፤ ከዚያም ጥቂት ፈቀቅ ብለው ዳግመኛ ጣሉ፤ በሰው ቁመትም ዐሥራ አምስት አገኙ። 29 ድንጋያማ በሆነ ቦታም እንዳይወድቁ ፈሩ፤ ስለዚህም ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቅ በባሕሩ ላይ ጣሉ፤ ፈጥኖ እንዲነጋም ጸለዩ። 30 ከዚህ በኋላም ቀዛፊዎቹ ከመርከብ ሊኮበልሉ በወደዱ ጊዜ ወደ ኋላ ሊመለሱ ከምድር ላይ ሆነው መርከባቸውን የሚያጠናክሩ መስለው ጀልባቸውን ወደ ባሕር አወረዱ። 31 ጳውሎስም ይህን ባየ ጊዜ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮቹ፥ “እነዚህ ቀዛፊዎች በመርከብ ውስጥ ከሌሉ መዳን አትችሉም” አላቸው። 32 ወታደሮችም ወዲያውኑ ተነሥተው የታንኳዪቱን ገመድ ቈርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት። 33 ሊነጋም በጀመረ ጊዜ ጳውሎስ እህል እንዲበሉ ሁሉንም ማለዳቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “እህል ከተዋችሁ ዛሬ ዐሥራ አራት ቀን ነው። 34 አሁንም እሺ በሉኝና ምግብ ብሉ፤ ራሳችሁንም አድኑ፥ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጕር እንኳ አትጠፋምና።” 35 ይህንም ተናግሮ ኅብስቱን አንሥቶ በሁሉም ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ። 36 ሁሉም ተጽናኑ፤ እህልም ቀመሱ። 37 በመርከቡ ውስጥ የነበሩትም ቍጥራቸው ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበር። 38 በልተውም በጠገቡ ጊዜ በመርከቡ ውስጥ የነበረውን ስንዴ ወደ ባሕር ጣሉት፤ መርከቡንም አቃለሉ። 39 በነጋ ጊዜም ቀዛፊዎች ቦታውን አልለዩም፤ የሚሄዱበትንም አላወቁም፤ ነገር ግን ለባሕሩ አቅራቢያ የሆነውን የደሴት ተራሮች አዩ፤ መርከባቸውንም ወደ እዚያ ሊያስጠጉ ፈለጉ። 40 መልሕቁንም ፈትተው በባሕር ላይ ጣሉት፤ የሚያቆሙበትንም አመቻችተው እንደ ነፋሱ አነፋፈስ መጠን ትንሹን ሸራ ሰቀሉ፤ ወደ ባሕሩ ዳርቻም ሄድን። 41 መርከቢቱም በሁለት ታላላቅ ድንጋዮች መካከል ተቀረቀረች፤ ባሕሩም ጥልቅ ነበረ። ከወደፊቷም ተያዘች፤ አልተንቀሳቀሰችምም፤ ከሞገዱም የተነሣ በስተኋላ በኩል ጎንዋን ተሰብራ ተጐረደች፤ ቀዛፊዎችም ወደፊት ሊገፉአት አልቻሉም። 42 ወታደሮቹም ዋኝተው እንዳያመልጡ እስረኞችን ለመግደል ተማከሩ። 43 የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ሊያድነው ወድዶአልና ምክራቸውን እንቢ አለ፤ ዋና የሚያውቁትንም ዋኝተው ወደ ምድር እንዲወጡ አዘዛቸው። 44 የቀሩትም በመርከቡ ስብርባሪ ዕንጨትና በሳንቃው ላይ ተሻገሩ፤ ሌሎችም በመርከቡ ገመድ ላይ እየተንጠላጠሉ ተሻገሩ፤ ሁሉም እንዲህ ባለ ሁኔታ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ። |