ሮሜ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከኀጢአት ተለይቶ በክርስቶስ መኖር 1 እንግዲህ ምን እንላለን? የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እንሥራን? አይደለም። 2 ከኀጢአታችን የተለየን እኛ እንግዲህ እንዴት ዳግመኛ በእርስዋ ጸንተን መኖር እንችላለን? 3 ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቅን እኛ ሁላችን በሞቱ እንደ ተጠመቅን ሁላችሁ ይህን ዕወቁ። 4 በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደ ተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን። 5 በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን። 6 ነገር ግን የኀጢአትን ሥጋ ይሽር ዘንድ ከእርሱ ጋር የተሰቀለው አሮጌው ሰውነታችን እንደ ሆነ ይህን እናውቃለን፤ ከእንግዲህ ወዲያ ዳግመና ለኀጢአት እንገዛ ዘንድ አንመለስም። 7 የሞተስ ከኀጢአት ነጻ ወጥቶአል። 8 ከክርስቶስ ጋር ከሞትንም ከእርሱ ጋር በሕይወት እንደምንኖር እናምናለን። 9 ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ፥ ዳግመኛም እንደማይሞት፥ እንግዲህ ወዲህም ሞት እንደማይገዛው እናውቃለን። 10 የሞተ አንድ ጊዜ ሞተ፤ በሞቱም ኀጢአትን ሻራት፤ የተነሣም ለእግዚአብሔር ተነሣ። 11 እንዲሁ እናንተም ራሳችሁን ለኀጢአት ምውታን አድርጉ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ለእግዚአብሔር ሕያዋን ሁኑ። 12 በዚህ በሚሞት ሰውነታችሁ ኀጢአትን አታንግሡአት፤ ለምኞቱም እሽ አትበሉት። 13 ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ፥ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኀጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት፤ ሰውነታችሁንም ለእግዚአብሔር የጽድቅ የጦር መሣሪያ አድርጉ። 14 እንግዲህ ኀጢአት አትገዛችሁም፤ የኦሪትን ሕግ ከመሥራት ወጥታችሁ ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ገብታችኋልና። ስለ መታዘዝ ምሥጢር 15 እንግዲህ ምን እንላለን? የኦሪትን ሕግ ከመሥራት ወጥተን ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ስለ ገባን ኀጢአት እንሥራን? አይደለም። 16 ለምትታዘዙለት፥ እሺ ለምትሉትም እናንተ አገልጋዮች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ለተባበራችሁለትስ ራሳችሁን እንደ አስገዛችሁ አታውቁምን? ኀጢአትንም እሺ ብትሉአት፥ ተባብራችሁም ብትበድሉ እናንት ለሞት ተገዢዎች ትሆናላችሁ፤ ጽድቅንም እሺ ብትሉአት ለበጎ ሥራም ብትተባበሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናችሁ። 17 የኀጢአት ተገዦች ስትሆኑ ምሳሌነቱ ለተሰጣችሁ ለምትማሩት ትምህርት ታዝዛችኋልና እግዚአብሔር ይመስገን። 18 አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ሁናችሁ ለጽድቅ ተገዝታችኋል። 19 ስለ ሰውነታችሁ ድካም በሰው ልማድ እነግራችኋለሁ፤ ዕወቁ፤ ቀድሞ ሰውነታችሁን ለኀጢአትና ለርኵሰት፥ ለዐመፃም እንደ አስገዛችሁ፥ እንዲሁ አሁንም ሰውነታችሁን ለጽድቅና ለቅድስና አስገዙ። 20 ለኀጢአት ትገዙ በነበረበት ጊዜ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። 21 በዚያን ጊዜ ሥራችሁም እነሆ፥ ዛሬ ታፍሩበታላችሁ፤ መጨረሻው ሞት ነውና። 22 ዛሬ ግን ከኀጢአት ነጻ ወጣችሁ፤ ራሳችሁንም ለጽድቅ አስገዛችሁ፤ ለቅድስናም ፍሬን አፈራችሁ፤ ፍጻሜው ግን የዘለዓለም ሕይወት ነው። 23 የኀጢአት ትርፍዋ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ጸጋ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም ሕይወት ነው። |