ኤርምያስ 31:10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አሕዛብ ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና፥ “እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ሕዝቦች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ሩቅ ባሉ የባሕር ጠረፎችም፣ ‘እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤ መንጋውንም እንደ እረኛ ይጠብቃል’ ብላችሁ ዐውጁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሕዛብ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውጁ፦ “እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል” በሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቦች ሆይ! አድምጡኝ፤ በሩቅ ጠረፎችም ቃሌን ዐውጁ፤ እኔ ሕዝቤን በትኜ ነበር፤ አሁን ግን እሰበስባቸዋለሁ፤ እረኛ መንጋውን እንደሚጠብቅም እጠብቃቸዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሕዛብ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና፦ እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ። |
ጽዮንም ሆይ፥ አምላክሽን አመስግኚ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፥ ልጆችሽንም በውስጥሽ ባርኮአልና።
እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፤ በምድር የቀሩትም ስለ እግዚአብሔር ክብር በአንድነት ደስ ይላቸዋል፤ የባሕርም ውኃ ይናወጣል።
በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ ዐጥር ያጥራል፤ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ።
ወደ ባሕር የምትወርዱ፥ በእርስዋም ውስጥ የምትጓዙ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ ከምድርም ዳርቻ ስሙን አክብሩ።
ከባቢሎን ውጡ፤ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ፤ ይህም ይሰማ፤ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና፥ “እግዚአብሔር ባርያውን ያዕቆብን ታድጎታል” በሉ።
ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤ የተርሴስም መርከቦች አስቀድመው ይመጣሉ፤ ልጆችሽ ስለ ከበረው ስለ እስራኤል ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ስም ወርቅና ብር ይዘው ከሩቅ ሀገር ይመጣሉ።
በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም ከሞት የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፥ ወደ ፉጥ፥ ወደ ሉድ፥ ወደ ሞሳሕ፥ ወደ ቶቤል፥ ወደ ኤላድ በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል ክብሬን ይናገራሉ።
“እስራኤል የባዘነ በግ ነው፤ አንበሶች አሳደዱት፤ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፥ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አጥንቱን ቈረጠመው።”
እስራኤልንም ወደ ማሰማርያው እመልሳለሁ፥ በቀርሜሎስና በባሳን፥ በኤፍሬም ተራራና በገለዓድም ይሰማራል፤ ነፍሱም ትጠግባለች።
ስለዚህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፤ ወደ ሀገሮችም እበትናቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ በመጡባቸው ሀገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል።
ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባትም ሀገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ።
በደመናና በጭጋግ ቀን እረኛ ከበጎቹ መካከል የተለየውን እንደሚፈልግ፥ እንደዚሁ በጎችን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጭጋግ ቀን ከተበተኑባቸው ሀገሮች ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ።
“ባሪያዬም ዳዊት በላያቸው ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ፤ ያደርጓትማል።
ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፤ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አደርግብሻለሁ፤ ከአንቺም የቀረውን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ።
የእስራትህም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በከተማዪቱ መካከል ሢሶውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ሢሶውንም ወስደህ ዙሪያውን በጎራዴ ትመታለህ፤ ሢሶውንም ወደ ነፋስ ትበትናለህ፤ እኔም በኋላቸው ጎራዴ እመዝዛለሁ።
እናንተንም በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ በሄዳችሁበትም ሁሉ ሰይፍ ታጠፋችኋለች፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፤ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።
ያዕቆብ ሆይ፥ ሁልንተናህን ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልንም ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፥ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፥ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፥ እነርሱም ይኖራሉ፥ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና።
እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርንም አማልክት ሁሉ ያከሳቸዋል፣ በአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በስፍራቸው ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።
በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፣ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፣ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ።
በዚያም ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ሕዝቡ መንጋ ያድናቸዋል፣ እነርሱም ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ፥ በምድሩም ላይ ይብለጨለጫሉ።
ስለ ሕዝብ ብቻ አልነበረም፤ የተበተኑትን የእግዚአብሔርንም ልጆች በአንድነት ይሰበስባቸው ዘንድ ነው እንጂ።