ዮሐንስ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ አልዓዛር 1 የማርያምና የእኅቷ የማርታ መንደር በሚሆን በቢታንያ ስሙ አልዓዛር የሚባል የታመመ አንድ ሰው ነበር። 2 ማርያም ግን ጌታችንን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጕርዋ ያሸችው ናት፤ ወንድምዋ አልዓዛርም ታሞ ነበር። 3 እኅቶቹም፥ “ጌታችን ሆይ፥ እነሆ፥ የምትወደው ታሞአል” ብለው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ላኩ። 4 ጌታችን ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አለ፥ “ይህ ደዌ በእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም።” 5 ጌታችን ኢየሱስም ማርታንና እኅቷን ማርያምን፥ አልዓዛርንም ይወዳቸው ነበር። 6 እንደ ታመመ በሰማ ጊዜM በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ። 7 ከዚህም በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ኑ፥ ወደ ይሁዳ ሀገር ደግሞ እንሂድ” አላቸው። 8 ደቀ መዛሙርቱም፥ “መምህር ሆይ፥ አይሁድ ሊወግሩህ ይሹ አልነበረምን? ዛሬ ደግሞ አንተ ወደዚያ ልትሄድ ትሻለህን?” አሉት። 9 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚሄድ አይሰናከልም፤ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና። 10 በሌሊት የሚሄድ ግን ይሰነካከላል፤ በውስጡ የሚያየው ብርሃን የለምና።” 11 ይህንም ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፤ ከዚህም በኋላ፥ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ” አላቸው። 12 ደቀ መዛሙርቱም፥ “አቤቱ፥ ከተኛስ ይነቃል፤ ይድናልም” አሉት። 13 ጌታችን ኢየሱስም ስለ ሞቱ ተናገረ፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት መስሎአቸው ነበር። 14 ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ገልጦ እንዲህ አላቸው፥ “አልዓዛር ሞተ። 15 ታምኑም ዘንድ እኔ በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እንሂድ።” 16 ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስም፥ ባልንጀሮቹን ደቀ መዛሙርት፥ “እኛም ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሂድ” አላቸው። ጌታችን አልዓዛርን ስለ ማስነሣቱ 17 ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቢታንያ ሄደ፤ ከዚያም በደረሰ ጊዜ ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። 18 ቢታንያም ለኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ቅርብ ነበረች። 19 ከአይሁድም ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርያምና ወደ ማርታ የሄዱ ብዙዎች ነበሩ። 20 ማርታም ጌታችን ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። 21 ማርታም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። 22 አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ።” 23 ጌታችን ኢየሱስም፥ “ወንድምሽስ ይነሣል” አላት። 24 ማርታም፥ “ሙታን በሚነሡባት በኋለኛዪቱ ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ” አለችው። ክርስቶስ ትንሣኤና ሕይወት ስለ መሆኑ 25 ጌታችን ኢየሱስም አላት፥ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል። 26 ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህንስ ታምኛለሽን?” 27 እርስዋም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ጌታችን ለአልዓዛር ስለ ማልቀሱ 28 ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅቷን ማርያምንም ቀስ ብላ ጠራችና፥ “እነሆ፥ መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል” አለቻት። 29 እርስዋም ይህን በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፤ ወደ እርሱም ሄደች። 30 ጌታችን ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። 31 ሊያጽናኑአት መጥተው በቤት ከእርስዋ ጋር የነበሩ አይሁድም ፈጥና ተነሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወንድምዋ ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሎአቸው ተከተሉአት። 32 ማርያምም ጌታችን ኢየሱስ ወደ አለበት ስፍራ ደረሰችና በአየችው ጊዜ ከእግሩ በታች ሰግዳ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። 33 ጌታችን ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ፥ ከእርስዋ ጋር የመጡ አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከ። 34 እርሱም፥ “የት ቀበራችሁት?” አለ፤ እነርሱም፥ “አቤቱ፥ መጥተህ እይ” አሉት። 35 ጌታችን ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። 36 አይሁድም፥ “ምን ያህል ይወደው እንደ ነበር እዩ” አሉ። 37 ከእነርሱም መካከል፥ “ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ዐይን ያበራው ይህ ሰው ይህስ እንዳይሞት ሊያደርግ ባልቻለም ነበርን?” ያሉ ነበሩ። 38 ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ በልቡ አዘነ፤ ወደ መቃብሩም ሄደ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበር፤ በላዩም ታላቅ ድንጋይ ተገጥሞበት ነበር። 39 ጌታችን ኢየሱስም፥ “ድንጋዩን አንሡ” አላቸው፤ የሟቹ እኅት ማርታም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አራት ቀን ሆኖታልና ፈጽሞ ሸትቶ ይሆናል” አለችው። 40 ጌታችን ኢየሱስም፥ “ብታምናስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ አላልሁሽም ነበርን?” አላት። 41 ድንጋዩንም አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አቅንቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ። 42 እኔም ዘወትር እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላሉት ሰዎች ይህን እናገራለሁ።” 43 ይህንም ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸና፥ “አልዓዛር፥ ና፤ ወደ ውጭ ውጣ” አለ። 44 ሞቶ የነበረውም እንደ ተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደ ታሰረ፥ ፊቱም በሰበን እንደ ተጠቀለለ ወጣ፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንግዲህስ ፍቱትና ተዉት ይሂድ” አላቸው። 45 ስለዚህ ከአይሁድም ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውን አይተው በእርሱ አመኑ። 46 ከእነርሱም መካከል ወደ ፈሪሳውያን ሄደው የከሰሱት ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውንም ሁሉ ነገሩአቸው። ስለ አይሁድ ምክር 47 የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፥ “እነሆ፥ ይህ ሰው ብዙ ተአምራት ያደርጋል፤ ምን እናድርግ? 48 እንዲሁ ብንተወውም ሁሉ ያምኑበታል፤ የሮም ሰዎችም መጥተው ሀገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል።” 49 በዚያችም ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተስ ምንም አታውቁም። 50 ምንም አትመክሩም፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናል።” 51 ይህንም ከልቡ የተናገረው አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሕዝብ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ። 52 ስለ ሕዝብ ብቻ አልነበረም፤ የተበተኑትን የእግዚአብሔርንም ልጆች በአንድነት ይሰበስባቸው ዘንድ ነው እንጂ። 53 ከዚያችም ቀን ጀምሮ የካህናት አለቆች ሊገድሉት ተማከሩ። ጌታችን ኢየሩሳሌምን ትቶ ስለ መሄዱ 54 ከዚያም ወዲያ ጌታችን ኢየሱስ በአይሁድ መካከል በግልጥ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ለምድረ በዳ አቅራቢያ ወደ ሆነች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 55 የአይሁድም የፋሲካ በዓል ቀርቦ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም ከበዓሉ አስቀድሞ ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከየሀገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ነበር። 56 አይሁድም ጌታችን ኢየሱስን ይፈልጉት ጀመር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው፥ “ምን ይመስላችኋል? ለበዓል አይመጣ ይሆን?” ተባባሉ። 57 የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ያለበትን የሚያውቅ ቢኖር ይይዙት ዘንድ እንዲያመለክታቸው አዘዙ። |