ኤርምያስ 27:9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የሐሰት ነቢያቶቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም ዐላሚዎቻችሁንና ባለ ራእዮቻችሁን፥ መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም ስለዚህ፣ የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም የሚሏችሁን ነቢያታችሁን፣ ሟርተኞቻችሁን፣ ሕልመኞቻችሁን፤ መናፍስት ጠሪዎቻችሁንና መተተኞቻቸሁን አትስሙ፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አታገለግሉም የሚሉአችሁን ነብዮቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነቢያታችሁንና በጥንቈላ፥ በመተት፥ ወይም የሙታን መናፍስትን በመሳብና ሕልም በማየት ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ እናውቃለን የሚሉትን ሁሉ አትስሙአቸው፤ እነርሱ ሁሉ የሚመክሩአችሁ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም ብለው ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን ነቢያቶቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፥ |
እነርሱም፥ “ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ” ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን?
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውም፤ የሐሰቱን ራእይ፥ ምዋርትንም፥ ከንቱንም ነገር፥ በልባቸውም የፈጠሩትን ይተነብዩላችኋል።”
ኀያል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ።
እነሆ ሐሰትን በሚያልሙ፥ በሚናገሩም፥ በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔም አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውምም፤ ለእነዚህ ሕዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም፥” ይላል እግዚአብሔር።
የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “በመካከላችሁ ያሉት የሐሰት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፤ ሕልም አላሚዎች አለምንላችሁ የሚሉአችሁን አትስሙ፥
በተገደሉት ኀጢአተኞች አንገት ላይ ያኖሩህ ዘንድ ከንቱ ራእይን ሲያዩልህ፥ በሐሰት ምዋርትም ሲናገሩልህ፥ በኀጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ ቀናቸው ደረሰ።
ተራፊም ከንቱነትን ተናግረዋልና፥ ምዋርተኞችም ውሸትን አይተዋልና፣ ሕልምንም የሚያዩ በሐሰት ተናግረዋል፥ በከንቱም ያጽናናሉ፣ እረኛም የላቸውምና እንደ በጎች ተቅበዝብዘዋል ተጨንቀውማል።
ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፣ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመመዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
በከንቱ ነገርም የሚያስታችሁ አይኑር፤ በእርሱ ምክንያት በከሓዲዎች ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መዓት ይመጣልና።
እርሱም፦ ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ብሎ የተናገረህ ምልክቱ ወይም ተአምራቱ ቢፈጸም፥
አንተ የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ ለአንተ ግን እንዲህ አይደለም፤ አምላክህ እግዚአብሔር አልፈቀደምና።
የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።”
ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።”