ዘዳግም 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የካህናትና ሌዋውያን ድርሻ 1 “ለሌዋውያን ካህናት፥ ለሌዊም ነገድ ሁሉ ከእስራኤል ጋር ድርሻና ርስት አይኑራቸው፤ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው መሥዋዕት ድርሻቸው ነው፤ እርሱን ይመገባሉ። 2 በወንድሞቻቸውም መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ እርሱ እንደ ተናገራቸው ርስታቸው እግዚአብሔር ነውና። 3 በሬ ወይም በግ ለመሥዋዕት ከሚያቀርቡት ሕዝብ የካህናቱ ወግ ይህ ይሆናል፤ ወርቹንና ሁለቱን ጕንጮቹን፥ ጨጓራውንም ለካህኑ ይሰጣሉ። 4 የእህልህን፥ የወይንህን፥ የዘይትህንም ቀዳምያት፥ አስቀድሞም የተሸለተውን የበግህን ጠጕር ለእርሱ ትሰጣለህ። 5 እርሱ ከልጆቹ ጋር በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ቁሞ ለዘለዓለም ያገለግል ዘንድ፥ በስሙም ይባርክ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከነገዶችህ ሁሉ መርጦታልና። 6 “አንድ ሌዋዊ ሰው ከሚቀመጥባቸው በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ካሉት ከተሞች ከአንዲቱ፥ በፍጹም ልብም ሊያገለግል እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ቢመጣ፥ 7 በእግዚአብሔር ፊት እንደሚቆሙት እንደ ወንድሞቹ እንደ ሌዋውያን ሁሉ በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ያገለግላል። 8 ከአባቶቹ ከብት ዋጋ ሌላ እንደ ባልንጀሮቹ ከመብል ድርሻውን ይወስዳል። ከአሕዛብ ልማድ ስለ መጠበቅ 9 “አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። 10 ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ አስማተኛም፥ መተተኛም፥ 11 በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም፥ በወፍም የሚያሟርት በአንተ ዘንድ አይገኝ። 12 ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያጠፋቸዋል። 13 አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን። 14 አንተ የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ ለአንተ ግን እንዲህ አይደለም፤ አምላክህ እግዚአብሔር አልፈቀደምና። እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንደሚነሣ 15 “አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ስሙት። 16 አምላካችሁን እግዚአብሔርን በኮሬብ በተሰበሰባችሁበት ቀን፦ ‘እንዳንሞት የአምላካችን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አንስማ፤ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አንይ’ ብላችሁ እንደ ለመናችሁት ሁሉ። 17 እግዚአብሔርም አለኝ፦ ለአንተ የተናገሩት ሁሉ ልክ ነው። 18 ከወንድሞቻቸው እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አኖራለሁ፤ እንደ አዘዝሁትም ይነግራቸዋል፤ 19 በስሜም በሚናገረው ሁሉ ያን ነቢይ የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀለዋለሁ። 20 ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን ቃል በስሜ የሚናገር ነቢይ፥ በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይም፥ እርሱ ይገደል። 21 በልብህም፦ እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እንዴት አውቃለሁ ብትል፥ 22 ያ ነቢይ በእግዚአብሔር ስም ከተናገረው ሁሉ ቃሉ ባይደርስ፤ እንደ ተናገረውም ባይሆን እግዚአብሔር ያን ቃል አልተናገረውም፤ ነቢዩ በሐሰት ተናግሮታልና አትስማው። |