ኤርምያስ 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስ የተሸከመው ቀንበር 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰንሰለትና ቀንበር ሥራ፤ በአንገትህም ላይ አድርግ፤ 3 ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ፥ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ፥ ወደ ሞዓብም ንጉሥ፥ ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ፥ ወደ ጢሮስም ንጉሥ፥ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ላክ።” 4 ለጌቶቻቸው እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፥ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሉ፦ 5 ምድሪቱን፥ በምድር ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኀይሌና በተዘረጋችው ክንዴ ፈጥሬአለሁ፤ ለዐይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ። 6 አሁንም ምድርን ሁሉ ለባሪያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ ያገለግሉትም ዘንድ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 7 የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጁ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት ለእርሱ ይገዙለታል። 8 “ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከንደነፆር የማይገዛውን፥ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፥ ያን ሕዝብ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የሐሰት ነቢያቶቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም ዐላሚዎቻችሁንና ባለ ራእዮቻችሁን፥ መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ 10 ከምድራችሁ እንዲያርቁአችሁ፥ እኔም እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተም እንድትጠፉ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና። 11 ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚገዛለትን ሕዝብ በሀገሩ ላይ እተወዋለሁ፤ እርሱም ያርሳታል፤ ይቀመጥባትማል።” 12 ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም ይህን ቃል ሁሉ ተናገርሁ፥ “ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ፤ ለእርሱና ለሕዝቡም ተገዙላቸው በሕይወትም ኑሩ። 13 ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛ ዘንድ እንቢ ስላለ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ለምን ትሞታላችሁ? 14 ሐሰተኛን ትንቢት ይናገሩላችኋልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ። 15 እኔ አልላክኋቸውምና፤ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተና ትንቢት የሚናገሩላችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።” 16 ለካህናትም ለዚህም ሕዝብ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሐሰተኛውን ትንቢት ይናገሩላችኋልና፦ የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ በቅርብ ጊዜ ከባቢሎን ይመለሳል የሚሉአችሁን የነቢያቶቻችሁን ቃል አትስሙ። 17 እነርሱን አትስሙ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ኑሩ፤ ይህችስ ከተማ ስለ ምን ባድማ ትሆናለች? 18 እነርሱ ግን ነቢያት ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት፥ በኢየሩሳሌምም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይሄዱ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር ይማለሉ።” 19 ስላልወሰዳቸው ዓምዶች፥ ስለ ባሕሩም፥ ስለ መቀመጫዎቹም፥ በዚች ከተማ ስለ ቀሩት ዕቃዎች ሁሉ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ 20 “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን አለቆች ሁሉ ማርኮ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ፥ 21 በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት፥ በኢየሩሳሌምም ስለ ቀሩት ዕቃዎች የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 22 ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፤ እስከምጐበኛቸው ቀን ድረስ በዚያ ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በዚያን ጊዜም ትወጣላችሁ፤ ወደዚህም ስፍራ ትመለሳላችሁ።” |