ዘፀአት 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እነሆ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። 2 ያዘዝሁህን ነገር ሁሉ አንተ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን የእስራኤልን ልጆች ከሀገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለፈርዖን ይንገረው። 3 እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፤ በግብፅ ምድርም ድንቄንና ተአምራቴን አበዛለሁ። 4 ፈርዖንም አይሰማችሁም፤ እጄንም በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ሕዝቤን በኀይሌ በታላቅ ፍርድ ከግብፅ ሀገር አወጣለሁ። 5 ግብፃውያንም እጄን በግብፅ ላይ በዘረጋሁ ጊዜ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከመካከላቸው በአወጣሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” 6 ሙሴና አሮንም እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7 ፈርዖንንም በተናገሩት ጊዜ ሙሴ ሰማንያ ዓመት ሆኖት ነበር፤ አሮንም ሰማንያ ሦስት ዓመት ሆኖት ነበረ። የአሮን ተአምራዊት በትር 8 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ 9 “ፈርዖን፦ ተአምራትንና ድንቅን አሳዩኝ ሲላችሁ፥ ወንድምህ አሮንን፦ ‘በትርህን ወስደህ በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት ጣላት’ በለው፤ እባብም ትሆናለች።” 10 ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት ጣለ፤ እባብም ሆነች። 11 ፈርዖንም ጠቢባንንና መተተኞችን ጠራ፤ የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ ደግሞ አደረጉ። 12 እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፤ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠች። 13 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ የፈርዖን ልብ ጸና፤ መስማትንም እንቢ አለ። ዐሥሩ መቅሠፍታት 1፥ የውኃ ወደ ደም መለወጥ 14 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ሕዝቡን እንዳይለቅቅ የፈርዖን ልብ ደነደነ። 15 ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነሆ፥ ወደ ውኃ ይወጣል፤ ትገናኘውም ዘንድ አንተ በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ እባብም ሆና የተለወጠችዉን በትር በእጅህ ትወስዳለህ። 16 እንዲህም ትለዋለህ፦ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር፦ በምድረ በዳ እንዲያመልኩኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆም፥ እስከ ዛሬ አልሰማህም። 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ፥ እኔ የወንዙን ውኃ በእጄ ባለችው በትር እመታለሁ፤ ውኃውም ወደ ደም ይለወጣል። 18 በወንዙም ያሉት ዓሦች ይሞታሉ፤ ወንዙም ይገማል፤ ግብፃውያንም የወንዙን ውኃ ለመጠጣት አይችሉም።” 19 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወንድምህ አሮንን፦ ‘በትርህን ውሰድ፤ በግብፅ ውኆች፥ በወንዞቻቸው፥ በመስኖዎቻቸውም፥ በኩሬዎቻቸውም፥ በውኃ ማከማቻቸውም ሁሉ ላይ እጅህን ዘርጋ’ በለው፤ ደምም ይሆናል፤” በግብፅም ሀገር ሁሉ በዕንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ሆነ። 20 ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን አነሣ፤ በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ። 21 በወንዙም የነበሩ ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ገማ፤ ግብፃውያንም ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉም፤ ደሙም በግብፅ ሀገር ሁሉ ሆነ። 22 የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ የፈርዖን ልብ ጸና፤ አልሰማቸውምም። 23 ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፤ በዚህም ሁሉ ልቡ አልተመለሰም። 24 ግብፃውያንም ሁሉ ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉምና በወንዙ ዳር ውኃ ሊጠጡ ቈፈሩ። 25 እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ። |