ዘፀአት 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ዕዳ አከፋፈል 1 “ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅ፥ ቢያርደው ወይም ቢሸጠው፥ በአንድ በሬ ፋንታ አምስት በሬዎች፥ በአንድ በግም ፋንታ አራት በጎች ይክፈል። 2 ሌባ ቤት ሲምስ ቢገኝ፥ እርሱም ቢመታ፥ ቢሞትም በመታው ሰው ላይ የደም ዕዳ አይሆንበትም። 3 ፀሐይ ግን ከወጣችበት የደም ዕዳ አለበት፤ የገደለው ይገደል፤ ሌባው ቢያዝ የሚከፍለውም ቢያጣ ስለ ሰረቀው ይሸጥ። 4 የሰረቀው ደኅና ሆኖ በእጁ ቢገኝ፥ በሬ ወይም በግ ቢሆን፥ የሰረቀውን ያህል ሁለት እጥፍ ይክፈል። 5 “የሰውን አዝመራ ከብቱን ያስበላ፥ የሌላ ሰው ወይንንም ያስበላ ሰው ቢኖር ግምቱን ይክፈል። የሰውን አዝመራ ፈጽሞ ቢያስበላ ግን በአጠገቡ ባለ አዝመራ ልክ ይክፈል፤ ወይንም ቢሆን በአጠገቡ ባለ ወይን ልክ ይክፈል። 6 “እሳት ቢነሣ ጫካውንም ቢይዝ፥ ዐውድማውንም፥ ክምሩንም ወይም ያልታጨደውን እህል ወይም እርሻውን ቢያቃጥል እሳቱን ያነደደው ይክፈል። 7 “ሰው በባልንጀራው ዘንድ ብር ወይም ሌላ ዕቃ እንዲጠብቅለት አደራ ቢያኖር ከቤቱም ቢሰረቅ፥ ሌባው ቢገኝ እጥፍ ይክፈል። 8 ሌባው ባይገኝ ባለቤቱ ወደ ፈጣሪ ፊት ይቅረብ፤ ባልንጀራው አደራ በአስቀመጠበት ገንዘብም ላይ እንዳልተተነኰለና ክፉ እንዳላሰበ ይማል። 9 ሰዎች ስለ በሬ ወይም ስለ አህያ ወይም ስለ በግ ወይም ስለ ልብስ ወይም ስለሌላ ስለ ጠፋ ነገር ቢካሰሱ፥ አንዱም፦ ‘ይህ የእኔ ነው’ ቢል፥ ክርክራቸው በፈጣሪ ፊት ይቅረብ፤ በፈጣሪ ፊት የተፈረደበት እርሱ ለባልንጀራው እጥፍ ይክፈል። 10 “ሰው በባልንጀራው ዘንድ አህያ ወይም በሬ ወይም በግ ወይም ሌላ እንስሳ እንዲጠብቅለት አደራ ቢያኖር፥ ማንም ሳያይ ቢሞት ወይም ቢጐዳ ወይም ቢማረክ፥ 11 በባልንጀራው ከብት ላይ እጁን እንዳልዘረጋ የእግዚአብሔር መሐላ በሁለታቸው መካከል ይሁን፤ የከብቱም ባለቤት ይህን ከተቀበለ፥ እርሱ ምንም አይክፈል። 12 ከእርሱም ዘንድ ቢሰረቅ ለባለቤቱ ይክፈል። 13 በምድረ በዳም አውሬ ቢበላው ውዳቂውን ያሳይ፤ አይክፈልም። 14 ሰው ከባልንጀራው አንዳች ቢዋስ ባለቤቱ ከእርሱ ጋር ሳይኖር ቢጎዳ፥ ወይም ቢሞት፥ ወይም ቢነጠቅ ፈጽሞ ይክፈለው። 15 ባለቤቱ ግን ከእርሱ ጋር ቢኖር አይክፈል፤ ቢከራየውም ኪራዩን ይክፈል። ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሕጎች 16 “ሰው ያልታጨችውን ድንግል ቢያስታት፥ ከእርስዋም ጋር ቢተኛ ሚስት አድርጎ ይውሰዳት። 17 አባቷም እርስዋን እንዳይሰጠው ፈጽሞ እንቢ ቢል እንደ ደናግል ማጫ ያህል ማጫዋን ይስጠው። 18 “ከመተተኛ ጋር አንድ አትሁኑ። 19 “ከእንስሳ የሚደርስ ሁሉ ሞትን ይሙት። 20 “ከእግዚአብሔር ብቻ በቀር ለአማልክት የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ። 21 እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድሉት፤ ግፍም አታድርጉበት። 22 መበለቲቱንና ድሀ-አደጎቹን አታስጨንቁአቸው። 23 ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸታቸውን ፈጽሞ እሰማለሁ፤ 24 ቍጣዬም ይጸናባችኋል፤ በሰይፍም አስገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁም መበለቶች፥ ልጆቻችሁም ድሀ-አደጎች ይሆናሉ። 25 “ከአንተ ጋር ለተቀመጠው ለድሃው ወገንህ ብር ብታበድረው፥ አታስጨንቀው፤ አራጣም አታስከፍለው። 26 የባልንጀራህን ልብስ ለመያዣ ብትወስድ ፀሐይ ሳትገባ መልስለት፤ 27 ልብሱ ነውና፥ ዕርቃኑንም የሚሸፍንበት ይህ ብቻ ነውና፤ የሚተኛበትም ሌላ የለውምና፤ ወደ እኔም ቢጮኽ ፈጥኜ እሰማዋለሁ፤ መሓሪ ነኝና። 28 “ፈራጆችን አትስደብ፥ የሕዝብህንም አለቃ ክፉ አትናገረው። 29 የአውድማህንና የወይንህንም መጀመሪያ ለማቅረብ አትዘግይ፤ የልጆችህንም በኵር ትሰጠኛለህ። 30 እንዲሁም በበሬዎችህና በበጎችህ፥ በአህያህም ታደርገዋለህ፤ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን ለእኔ ትሰጠዋለህ። 31 ቅዱስ ወገን ትሆኑልኛላችሁ፤ ስለዚህ አውሬ የገደለውን ሥጋ ለውሻ ጣሉት እንጂ አትብሉት። |