ኢሳይያስ 65:15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ስማችሁንም እኔ ለመረጥኋቸው ሕዝቤ ጥጋብ አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ያጠፋችኋል፤ ባሪያዎች ግን በሐዲስ ስም ይጠራሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ስማችሁንም፣ የተመረጠው ሕዝቤ ርግማን እንዲያደርገው ትተዋላችሁ፤ ጌታ እግዚአብሔር ይገድላችኋል፤ ለአገልጋዮቹ ግን ሌላ ስም ይሰጣቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ አገልጋዮቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እኔ ጌታ እግዚአብሔርም እናንተን ለሞት አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የእናንተም ስም በእኔ ተመራጮች ዘንድ መራገሚያ ይሆናል፤ ለአገልጋዮቼ ግን የተለየ ስም እሰጣቸዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። |
አሕዛብ ጽድቅሽን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ።
እኔም ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ ሁላችሁም በሰይፍ ትገደላላችሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገር አደረጋችሁ፤ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራኋችሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና።”
ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፤ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ሕይወት ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረዥም ዘመን ደስ ይላቸዋል።
የያዕቆብን ዘርና የይሁዳን ዘር አመጣለሁ፤ የተቀደሰው ተራራዬንም ይወርሳሉ፤ እኔ የመረጥኋቸውና ባሪያዎችም ይወርሱአታል፤ በዚያም ይኖራሉ።
እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ እንደ እሳት ይመጣል፤ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ።
በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ፥ ለጥላቻና ለርግማን ይሆኑ ዘንድ በምድር መንግሥታት ሁሉ እንዲበተኑ አደርጋለሁ።
ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ፈጽሞ ምድረ በዳ ይሆኑ ዘንድ፥ ለርግማንም አደርጋቸው ዘንድ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች፥ ነገሥታቷንም፥ አለቆችዋንም አጠጣኋቸው።
በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም አሳድዳቸዋለሁ፤ ባሳደድሁባቸውም አሕዛብ ሁሉ ዘንድ ለርግማንና ለጥፋት፥ ለማፍዋጫም፥ ለመሰደቢያም እንዲሆኑ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፦ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ እግዚአብሔር ያድርግህ የምትባል ርግማንን ያነሣሉ፤
“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ቍጣዬና መቅሠፍቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ፈሰሰ፥ እንዲሁ ወደ ግብፅ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይፈስስባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለጥፋት ለስድብና ለርግማን ትሆናላችሁ፤ ይችንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩአትም።
ወደ ግብፅም ይገቡ ዘንድ፥ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ቅሬታ እወስዳለሁ፤ ሁሉም ይጠፋሉ፤ በግብፅም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለጥፋት፥ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ።
ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ፤ እንዲጠፋም አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፣ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ።
በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት አብረው ተቀመጡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ።
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፤ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፤ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።