Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 65 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ፦ “አለሁኝ፥ አለሁኝ” አልኩት።

2 መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ።

3 ይህ ሕዝብ ዘወትር በፊቴ ቁጣን ይቀሰቅሳሉ፥ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ፥ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፥

4 በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፥ ምሽቱንም በስውርም ስፍራ የሚያሳልፉ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። ማሰሮዎቻቸው በረከሰ ነገር የተሞሉ ናቸው።

5 እነርሱም፦ “ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ” ይላሉ፤ እነዚህ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት፥ በአፍንጫዬ ስር የምታልፍ ጢስ ናቸው።

6 እነሆ፥ በፊቴ እንዲህ ተጽፎአል፦ “ዝም አልልም፤ ነገር ግን እንደ ሥራው እሰጠዋለሁ፤ የእጃቸውንም እከፍላቸዋለሁ።

7 በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፥ ስለዚህ አስቀድመው ለሠሩት ሥራቸውን የእጃቸውን እሰጣቸዋለሁ።”

8 ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ፥ “በረከት በእርሷ ላይ አለና አታጥፉት” እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፋ ስለ አገልጋዮቼ እንዲሁ አደርጋለሁ።

9 ከያዕቆብም ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኳቸው ይወርሷታል፥ አገልጋዬቼም በዚያ ይኖራሉ።

10 ለፈለገኝ ሕዝቤ ሳሮን የበጎች ማሰማርያ፥ የአኮር ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ይሆናል።

11 እናንተን ጌታን የተዋችሁትን ግን፥ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፥ ዕጣ ፋንታ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፥ ዕድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን የቀዳችሁትን፥

12 እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፥ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፥ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራኋችሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝም፤ በተናገርኩም ጊዜ አልሰማችሁኝም።

13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤

14 እነሆ፥ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፥ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ።

15 ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ አገልጋዮቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል።

16 እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፥ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ ምክንያቱም የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአል፥ ከዓይኔም ተሰውሮአል።


የከበረው አዲስ ፍጥረት

17 እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁ፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ትውስታቸውም አይኖርም።

18 ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘለዓለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና።

19 እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም።

20 ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጎልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ የመቶ ዓመት ሳይሆነው የሚሞት እንደተረገመ ኃጢአተኛ ይታያል።

21 ቤትም ይሠራሉ ይኖሩበታል፤ ወይንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ።

22 ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።

23 እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።

24 እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፥ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ።

25 ተኩላና ጠቦት በአንድነት ይሠማራሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ጉዳት አያደርሱም፥ አያጠፉምም፥ ይላል ጌታ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos