ኢሳይያስ 1:17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) መልካም መሥራትን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፤ የተገፋውን አድኑ፤ ለድሃአደጉ ፍረዱለት፤ ስለ መበለቲቱም ተሙአገቱ።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፣ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፤ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም መልካም ማድረግንም ተማሩ፤ ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ የተጨቈኑትን ታደጉ፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት ጠብቁ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ ስሙ።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ክፉ ማድረግን ተዉ፥ መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። |
አለቆችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፤ ፍርድንም ሊያጣምሙ ይፈልጋሉ፤ ለሙት ልጅ አይፈርዱም፤ የመበለቲቱንም አቤቱታ አያዳምጡም።
መበለቶች ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ የሙት ልጆችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሃውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ ወዮላቸው!
ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለም ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን የበደልን እስራት ፍታ፤ ጠማማውን ሁሉ አቅና፤ የተጨነቀውንም ሁሉ አድን፤ የዐመፃ ደብዳቤንም ተው።
የዳዊት ቤት ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይነድድና ማንም ሳያጠፋው እንዳያቃጥል፥ በማለዳ ፍርድን አድርጉ፤ የተነጠቀውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተነጠቀውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሃአደጉን፥ ባልቴቲቱንም አትበድሉ፤ አታምፁባቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ።
ደግሞም፦ እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ሥራችሁንም አሳምሩ፤ ታገለግሉአቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ እያልሁ ባሪያዎችን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም፤ እኔንም አልሰማችሁኝም።
የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስንም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ስለ ምን ትሞታላችሁ?
በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ።
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል አለቆች ሆይ! ይብቃችሁ፤ ግፍንና ዐመፅን አስወግዱ፤ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?
እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፥ ትሕትናንም ፈልጉ፣ ምናልባት በእግዚአብሔር ቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።
የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፣ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፣
ሌዋዊዉም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በከተማህ ውስጥ ያለ መጻተኛ፥ ድሃ-አደግም፥ መበለትም መጥተው ይበላሉ፤ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው።
ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።