ኤርምያስ 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኤርምያስ መልእክት ለይሁዳ ቤተ መንግሥት 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድ፤ በዚያም ይህን ቃል ተናገር፥ እንዲህም በል፦ 2 በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! አንተና አገልጋዮችህ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተነጠቀውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሃአደጉን፥ ባልቴቲቱንም አትበድሉ፤ አታምፁባቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ። 4 ይህንም ነገር ብታደርጉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፥ በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ፤ እነርሱም፥ አገልጋዮቻቸውም፥ ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ። 5 ነገር ግን ይህን ቃል ባትሰሙ፥ ይህ ቤት ወና እንዲሆን በራሴ ምያለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። 6 እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና፥ “አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድና እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ፤ በርግጥ ምድረ በዳና ማንም የማይቀመጥባቸው ከተሞች አደርግሃለሁ። 7 የሚአጠፋህን ሰው በአንተ ላይ አመጣለሁ፤ የሚያምረውን ዛፍህንም በምሳር ይቈርጣል፤ በእሳትም ያቃጥላል። 8 ብዙ አሕዛብም በዚች ከተማ ላይ ያልፋሉ፤ ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን፦ እግዚአብሔር በዚች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደረገ? ይላሉ። 9 እነርሱም፦ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ፥ ስለ አመለኳቸውም ነው ብለው ይመልሳሉ።” 10 ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና፥ የተወለደባትንም ሀገር አያይምና ለሚወጣ እጅግ አልቅሱ እንጂ ለሞተ አታልቅሱ፤ አትዘኑለትም። 11 በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ ስለ ነገሠው፥ ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣውና ስለማይመለሰው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ፥ ስለ ሳሌም እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ 12 “በተማረከበት ሀገር ይሞታል፤ እንግዲህም ወዲህ ሀገሩን አያይም።” 13 ቤቱን በዐመፅ፥ አዳራሹንም ያለ እውነት ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው ወዮለት! 14 “ለራሴ ሰፊ ቤት፥ ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ ለሚል፥ መስኮትንም ለሚያወጣ፥ በዝግባም ሥራ ለሚያስጌጥ፥ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት፤ 15 በአባትህ ዝግባ አዳራሽ ስለ ሠራህ በውኑ ትነግሣለህን? በውኑ አባትህ አይበላና አይጠጣም ነበርን? ፍርድንና ጽድቅንስ አያደርግም ነበርን? በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር። 16 የድሃውንና የችግረኛውን ፍርድ ይፈርድ ነበር፤ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር። 17 እነሆ ዐይንህና ልብህ መልካም አይደለም፤ ነገር ግን ለቅሚያ፥ ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ፥ ግድያንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ነው።” 18 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፥ “ወንድሜ ሆይ፥ ወዮ! ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! እያለ የሚያለቅስለት ለሌለው ለዚያ ሰው ወዮለት! 19 አህያም እንደሚቀበር ይቀበራል፤ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ፥ በውራጅ ጨርቅ ተጠቅልሎ ይጣላል።” 20 ወዳጆችሽ ሁሉ ጠፍተዋልና ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ፤ በባሳንም ላይ ድምፅሽን አንሺ፤ በባሕሩም ማዶ ጩኺ። 21 በጐሰቈልሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፤ አንቺም፦ አልሰማም አልሽ፤ ከሕፃንነትሽ ጀምሮ ቃሌን አለመስማትሽ መንገድሽ ነው። 22 በግ ጠባቂዎችሽን ሁሉ ነፋስ ይወስዳቸዋል፤ ወዳጆችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ ክፋትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ፤ በወዳጆችሽም ፊት ቷረጃለሽ። 23 አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፥ በዝግባ ዛፍም ውስጥ የምታለቅሺ ሆይ! ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕማም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ትጨነቂያለሽ! በኢዮአቄም ላይ የደረሰ የእግዚአብሔር ፍርድ 24 “እኔ ሕያው ነኝ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን ሆይ፥ አንተን በሰወርሁበት ቀኝ እጄ እንዳለ ማሕተም ነበርህ፤ እንግዲህ ወዲህ ግን እንደማትኖር እኔ ሕያው ነኝ፤” ይላል እግዚአብሔር፤ 25 ነፍስህንም ለሚሹአት፥ ከፊታቸውም የተነሣ ለምትፈራቸው እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆርና ለከለዳውያንም እጅ እሰጥሃለሁ። 26 አንተንም፥ የወለደችህን እናትህንም ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ ሀገር እጥላችኋለሁ፤ በዚያም ትሞታላችሁ። 27 ነፍሳችሁም ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አትመለሱም። 28 ኢኮንያን ተዋረደ፤ ለምንም እንደማይጠቅም የሸክላ ዕቃ ሆነ፤ እርሱንና ዘሩን ወደማያውቀው ሀገር ወርውረው ጥለውታልና። 29 ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ። 30 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዘመኑ አይከናወንምና፥ ከዘሩም በዳዊት ዙፋን የሚቀመጥ አይነሣምና፥ እንግዲህ ወዲህም ለይሁዳ ገዢ አይሾምምና ይህን ሰው እንደ ሞተ ቍጠሪው” አለ። |