ኤርምያስ 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ኢየሩሳሌም መያዝ የተነገረ ትንቢት 1 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና የካህኑን የመዕሴይን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ኤርምያስ በላከ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፦ እንዲህም አለ፦ 2 “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋን ዘንድ መጥቶአልና ከእኛ ይመለስ ዘንድ፥ ምናልባትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ እንደ ሆነ ስለ እኛ፥ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅ።” 3 ኤርምያስም እንዲህ አላቸው፥ “የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት፦ 4 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የባቢሎንን ንጉሥ በቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን የጦር መሣሪያችሁን እሰጣችኋለሁ፤ እነዚያንም በዚህች ከተማ መካከል እሰበስባቸዋለሁ። 5 እኔም በተዘረጋች እጅና በብርቱ ክንድ፥ በቍጣና በመዓት፥ በታላቅም መቅሠፍት አወጋችኋለሁ። 6 በዚህችም ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ሰዎችንና እንስሶችን እመታለሁ፤ በጽኑም ቸነፈር ይሞታሉ። 7 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና አገልጋዮቹን፥ ከቸነፈርና ከሰይፍ፥ ከራብም በዚህች ከተማ የቀሩትን ሕዝቡንም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፤ አይራራላቸውም፤ አይምራቸውም።” 8 ለዚህም ሕዝብ እንዲህ በል፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አድርጌአለሁ። 9 በዚህች ከተማ ውስጥ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፤ ሰውነቱም ምርኮ ትሆናለች። 10 ለመልካም ሳይሆን ለክፉ ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁና፤ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል።” 11 የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 12 የዳዊት ቤት ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይነድድና ማንም ሳያጠፋው እንዳያቃጥል፥ በማለዳ ፍርድን አድርጉ፤ የተነጠቀውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ። 13 እነሆ በሜዳ ላይ ባለው ድንጋያማ ሸለቆ የምትቀመጥ ሆይ! እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ እናንተም፦ የሚያስደነግጠን ወይም ወደ መኖሪያችን የሚገባ ማን ነው? የምትሉ ሆይ! እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፤ 14 እንደ ሥራችሁም ፍሬ እቀጣችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር በዱርዋም ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፤ በዙሪያዋም ያለውን ሁሉ ይበላል።” |