ሕዝቅያስም፥ “አሁን እጃችሁን ለእግዚአብሔር አንጽታችሁ ቅረቡ፤ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ” ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ።
ዕብራውያን 13:15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? አዲሱ መደበኛ ትርጒም ስለዚህ ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንግዲህ ዘወትር ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት አድርገን በእርሱ በኩል እናቅርብለት። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንግዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የምስጋና መሥዋዕት ዘወትር ለእግዚአብሔር እናቅርብ፤ ይህም ስለ ስሙ በሚመሰክሩት ከንፈሮች የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት። |
ሕዝቅያስም፥ “አሁን እጃችሁን ለእግዚአብሔር አንጽታችሁ ቅረቡ፤ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ” ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ።
ካህናቱም በየሥርዐታቸው ሌዋውያኑም ደግሞ፥ “ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” የሚለውን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ፥ ንጉሡ ዳዊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሠራውን የእግዚአብሔርን የዜማ ዕቃ ይዘው ቆመው ነበር፤ ካህናቱም በፊታቸው መለከት ይነፉ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመው ነበር።
ደግሞ፥ “ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” እያሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት በተመሠረተ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩ በታላቅ ድምፅ ዘመሩ።
እግዚአብሔርም በታላቅ ደስታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በዚያ ቀን ትልቅ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ደስም አላቸው፤ ሴቶቹና ልጆቹም ደግሞ ደስ አላቸው፤ ደስታቸውም በኢየሩሳሌም ከሩቅ ተሰማ።
የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ሰዎች ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የዚያችን ምድር ምርኮኞች ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር።
የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል፥ ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም።”
ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም የስንዴ ዱቄት ያቀርባል።
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “አባት ሆይ! የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ።
በዚያች ሰዓትም ጌታችን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ደስ አለው፤ እንዲህም አለ፥ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከዐዋቂዎችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥኸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲሁ ሆኖአልና።
ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
ወንድሞቻችን፥ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው።
ስለ ሰውነታችሁ ድካም በሰው ልማድ እነግራችኋለሁ፤ ዕወቁ፤ ቀድሞ ሰውነታችሁን ለኀጢአትና ለርኵሰት፥ ለዐመፃም እንደ አስገዛችሁ፥ እንዲሁ አሁንም ሰውነታችሁን ለጽድቅና ለቅድስና አስገዙ።
ስለዚህ የማይናወጥ መንግሥትን ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሀት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ።
ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል፤ ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል።
እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።
ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ “እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኀይል ነው” ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።