ነህምያ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሌዋውያንና ካህናት ስም ዝርዝር 1 ከሰላትያል ልጅ ከዘሩባቤልና ከኢያሱ ጋር የወጡት ካህናትና ሌዋውያን እነዚህ ነበሩ፤ ሠራህያ፥ ኤርምያስ፥ ዔዝራ፤ 2 አማርያ፥ መሎክ፥ ሐጡስ፥ 3 ሴኬንያ፥ ሬሁም፥ ሜራሞት፤ 4 አዶ፥ ጌንቶን፥ አብያ፤ 5 ሚያሚን፥ መዓድያ፥ ቤልጋ፤ 6 ሰማዕያ፥ ዮያሪብ፥ ዮዳኤያ፤ 7 ሳሎም፥ ዓሞቅ፥ ሔልቅያስ፥ ኢዳዕያ፤ እነዚህ በኢያሱ ዘመን የካህናቱና የወንድሞቻቸው አለቆች ነበሩ። 8 ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ በንዊ፥ ቀድምኤል፥ ሰራብያ፥ ይሁዳ፥ ከወንድሞቹም ጋር በመዘምራን ላይ የተሾመ ማታንያ። 9 ወንድሞቻቸውም በቅቡቅያና ዑኒ በየሰሞናቸው በአንጻራቸው ነበሩ። 10 ኢያሱም ዮአቂምን ወለደ፤ ዮአቂምም ኤሊያሴብን ወለደ፤ ኤሊያሴብም ዮሐዳን ወለደ፤ 11 ዮሐዳም ዮናታንን ወለደ፤ ዮናታንም ይዱዕን ወለደ። 12 በዮአቂምም ዘመን የአባቶች ቤቶች አለቆች ወንድሞቹ ካህናቱ ነበሩ፤ ከሠራያ ምራያ፥ ከኤርምያስ ሐናንያ፤ 13 ከዕዝራ ሜሱላም፥ ከአማርያ ዮሐናን፤ 14 ከማሎክ ዮናታን፥ ከሴብንያ ዮሴፍ፤ 15 ከሐሪም ዓድና፥ ከመራዮት ሔልቃይ፤ 16 ከአዶ ዘካርያስ፥ ከጌንቶን ሜሱላም፤ 17 ከአብያ ዝክሪ፥ ከሚያሚንና ከሞዓድያ፥ ፈልጣይ፤ 18 ከቤልጋ ሳሙኣ፥ ከሰማዕያ ዮናታን፤ 19 ከዮያሬብ መትናይ፥ ከዮዳኤያ ኦዚ፤ 20 ከሳላይ ቃላይ፥ ከዓሞቅ ዔቤር፤ 21 ከኬልቅያስ ሐሳብያ፥ ከኢዳዕያ ናትናኤል። 22 ከሌዋውያኑም በኤልያሴብና በዮሐዳ፥ በዮሐናንና በያዱዕ ዘመን የአባቶች ቤቶች አለቆች ተጻፉ፤ ካህናቱም በፋርሳዊው በዳርዮስ መንግሥት ዘመን ተጻፉ። 23 የሌዊ ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆች እስከ ኤልያሴብ ልጅ እስከ ዮሐናን ዘመን ድረስ በታሪክ መጽሐፍ ተጻፉ። 24 የሌዋውያኑም አለቆች አሳብያ፥ ሰርብያ፥ ኢያሱ፥ የቀድምኤልም ልጆች፥ ወንድሞቻቸውም እንደ እግዚአብሔር ሰው እንደ ዳዊት ትእዛዝ በየሰሞናቸው በእነርሱ ፊት ያከብሩና ያመሰግኑ ነበር። 25 መታንያ፥ በቅቡቅያ፥ አብድያ፥ ሜሱላም፥ ጤልሞን፥ ዓቁብ በበሮች አጠገብ የሚገኙትን ዕቃ ቤቶች ለመጠበቅ በረኞች ነበሩ። 26 እነዚህም በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ልጅ በዮአቂም በአለቃውም በነህምያ፥ በጸሓፊውም በካህኑ በዕዝራ ዘመን ነበሩ። የኢየሩሳሌም ቅጽር ምረቃ በዓል 27 የኢየሩሳሌምም ቅጥር በተመረቀ ጊዜ ምረቃውን በደስታና በምስጋና፥ በመዝሙርም፥ በጸናጽልም፥ በበገናም፥ በመሰንቆም ለማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸው ዘንድ ሌዋውያኑን በየስፍራቸው ሁሉ ፈለጉ። 28 የመዘምራኑም ልጆች ከኢየሩሳሌም ዙርያና ከሌሎችም መንደሮች ተሰበሰቡ። 29 ከቤት ጌልጋልና ከጌባ፥ ከአዝማዊትም እርሻ መዘምራኑ በኢየሩሳሌም ዙርያ ለራሳቸው መንደሮች ሠርተዋልና። 30 ካህናቱና ሌዋውያኑም ራሳቸውን አነጹ፤ ሕዝቡንም፥ በረኞችንም ቅጥሩንም አነጹ። 31 የይሁዳንም አለቆች ወደ ቅጥሩ አወጣኋቸው፤ አመስጋኞቹንም በሁለት ታላላቅ ተርታ አቆምኋቸው፤ የአንዱም ተርታ ሰዎች ወደ ቀኝ በቅጥሩ ላይ ወደ ጉድፍ መጣያው በር ሄዱ። 32 ከእነርሱም በኋላ ሆሴዕ የይሁዳም አለቆች እኩሌታ፤ 33 ዓዛርያ፥ ዕዝራ፥ ሜሱላም፥ 34 ይሁዳ፥ ብንያም፥ ሰማዕያ፥ ኤርምያስ፤ 35 መለከትም ይዘው ከካህናቱ ልጆች አያሌዎች፥ የአሳፍም ልጅ የዘኩር ልጅ የሚካያ ልጅ የመታንያ ልጅ የሰማዕያ ልጅ የዮናታን ልጅ ዘካርያስ፤ 36 ወንድሞቹም ሰማዕያ፥ አዘርኤል፥ ማዕላይ፥ ጌላላይ፥ መዓይ፥ ናትናኤል፥ ይሁዳ፥ አናኒ የእግዚአብሔርን ሰው የዳዊትን የዜማውን ዕቃ ይዘው ሄዱ፤ ጸሓፊውም ዕዝራ በፊታቸው ነበረ። 37 በምንጭም በር አቅንተው ሄዱ፤ በዳዊትም ከተማ ደረጃ፥ በቅጥሩም መውጫ፥ ከዳዊትም ቤት በላይ እስከ ውኃው በር ድረስ በምሥራቅ በኩል ሄዱ። 38 ሁለተኛውም የአመስጋኞቹ ክፍል ወደ ግራ ሄደ፤ እኔና የሕዝቡም እኩሌታ በስተኋላቸው ነበርን፤ በቅጥሩም ላይ፥ በእቶኑ ግንብ በላይ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ፥ 39 ከኤፍሬምም በር በላይ፥ በአሮጌው በርና በዓሣ በር፥ በአናንኤልም ግንብ፥ በሃሜአ ግንብ እስከ በጎች በር ድረስ ሄዱ፤ በዘበኞችም በር አጠገብ ቆሙ። 40 እንዲሁ ሁለቱ የአመስጋኞች ክፍሎች በእግዚአብሔር ቤት ቆሙ፤ ከእነርሱም ጋር እኔና የአለቆች እኩሌታ ነበርን፤ 41 ካህናቱም ኤልያቄም፥ መዕሤያ፥ ሚንያሚን፥ ሚካያ፥ ኤልዮዔናይ፥ ዘካርያስ፥ ሐናንያ መለከት ይዘው፥ 42 መዕሤያ፥ ሰማዕያ፥ ኤልየዜር፥ ኦዚ፥ ዮሐናን፥ ሚልክያ፥ ኤላም፥ ኤዝር፥ መዘምራኑም በታላቅ ድምፅ ዘመሩ፤ አለቃቸውም ይዝረአያ ነበረ። 43 እግዚአብሔርም በታላቅ ደስታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በዚያ ቀን ትልቅ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ደስም አላቸው፤ ሴቶቹና ልጆቹም ደግሞ ደስ አላቸው፤ ደስታቸውም በኢየሩሳሌም ከሩቅ ተሰማ። 44 የይሁዳም ሕዝብ በአገልጋዮቹ ካህናትና ሌዋውያን ደስ ስላላቸው፥ የካህናቱንና የሌዋውያኑን ዕድል ፈንታ እንደ ሕጉ ከከተሞች እርሻዎች ያከማቹ ዘንድ ለቀዳምያት፥ ለዐሥራትም በየዕቃ ቤቶቹ ላይ በዚያ ቀን ሰዎችን ሾሙ። 45 እነርሱም መዘምራኑና በረኞቹም የአምላካቸውን ሥርዐት የመንጻታቸውን ሥርዐት እንደ ዳዊትና እንደ ልጁ እንደ ሰሎሞን ትእዛዝ ጠበቁ። 46 በዳዊትም ዘመን አሳፍ የመዘምራን አለቃ ነበር፤ እነርሱም እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር። 47 እስራኤልም ሁሉ በዘሩባቤልና በነህምያ ዘመን ለመዘምራኑና ለበረኞቹ ፈንታቸውን በየዕለቱ ይሰጡ ነበር፤ የተቀደሰውንም ነገር ለሌዋውያን ሰጡ፤ ሌዋውያኑም ከተቀደሰው ነገር ለአሮን ልጆች ሰጡ። |