ዘሌዋውያን 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ በደል መሥዋዕት ሕግ 1 “የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 2 የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት በግ በዚያ ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 3 ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ፥ በአንጀቱም ላይ ያለውን ስብ፤ 4 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ካህኑ ይለያል። 5 ካህኑም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል፤ እርሱም የበደል መሥዋዕት ነው። 6 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 7 የኀጢአት መሥዋዕት እንደ ሆነ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ ነው፤ በእነርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ይወስደዋል። 8 የሰውን የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቍርበት ለዚያው ካህን ይሆናል። 9 በእቶን የተጋገረው የእህል ቍርባን ሁሉ፥ በመቀቀያም ወይም በምጣድ የበሰለው ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል። 10 በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቍርባን ሁሉ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ ለእያንዳንዱም እኩል ይሆናል። ስለ ደኅንነት መሥዋዕት ሕግ 11 “ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 12 ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም የስንዴ ዱቄት ያቀርባል። 13 ለምስጋና የሚሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት በአቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል። 14 ከቍርባኑም ሁሉ የእግዚአብሔርን ድርሻ ከእነርሱ አንዱን ያነሣል። እርሱም የደኅንነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። 15 “ለምስጋና የሚሆነው የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋም ለእርሱ ነው፤ በሚቀርብበትም ቀን ይበሉታል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያተርፉም። 16 የቍርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ቀን ይብሉት፤ ከእርሱም የቀረውን በነጋው ይብሉት፤ 17 ከመሥዋዕቱም ሥጋ እስከ ሦስተኛው ቀን የሚቈየውን በእሳት ያቃጥሉታል። 18 በሦስተኛው ቀን ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርም፤ ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቍርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ከእርሱም የበላ ሰው ኀጢአቱን ይሸከማል። 19 “ርኩስ ነገር የሚነካውን ሥጋ አይብሉት፤ በእሳት ያቃጥሉት እንጂ። ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ግን ከሥጋው ይብላ። 20 ኀጢአት ሳለባት፥ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ የበላች ሰውነት፥ ያች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ። 21 ከርኩስ ሁሉ፥ ወይም ከረከሰው ሰው፥ ወይም ንጹሕ ካልሆነው እንስሳ የነካች ሰውነት፥ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ብትበላ፥ ያች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ።” ስብንና ደምን መብላት ስለማይገባ 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 23 “የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ። 24 የሞተውን ስብ፥ አውሬ የሰበረውንም ስብ ለሌላ ተግባር አድርጉት፤ እናንተ ግን አትብሉት፤ 25 ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ ያች የበላች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ። 26 በመኖሪያዎቻችሁ ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን አትብሉ። 27 ደም የምትበላ ሰውነት ሁሉ ያች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ።” ከደኅንነቱና ከሚቃጠለው መሥዋዕት የካህናት ዕድል ፈንታ 28 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 29 “የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ ለእግዚአብሔር የደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቍርባኑን ለእግዚአብሔር ከደኅንነቱ መሥዋዕት ያመጣል። 30 የእርሱ እጆች ለእግዚአብሔር የእሳቱን ቍርባን ያመጣሉ፤ ፍርምባውን በእግዚአብሔር ፊት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ በጉበቱ ላይ ያለውን መረብና የፍርምባውን ስብ ያመጣል። 31 ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ይጨምረው፤ ፍርምባውም ለአሮንና ለልጆቹ ይሁን። 32 ከደኅንነት መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን ለማንሣት ቍርባን እንዲሆን ለካህኑ ትሰጡታላቸሁ። 33 ከአሮንም ልጆች የደኅንነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርብ ለእርሱ ቀኝ ወርቹ እድል ፈንታው ይሆናል። 34 ፍርምባውንና የቀኝ ወርቹን ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕታቸው ወስጄአለሁ፤ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘለዓለም ሕግ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ሰጥቼአቸዋለሁ።” 35 እግዚአብሔርን በክህነት ያገለግሉት ዘንድ በተቀቡበት ቀን ለእግዚአብሔር ከሆነ ከእሳት ቍርባን የአሮንና የልጆቹ ሕግ ይህ ነው። 36 ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ሕግ እንዲሆን በቀባቸው ቀን የእስራኤል ልጆች ይሰጡአቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው። 37 የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን፥ የኀጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 38 እግዚአብሔር በሲና ምድረ በዳ ቍርባናቸውን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርቡ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው። |