ዘፍጥረት 1:26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም አለ፥ “ሰውን በአርኣያችንና በአምሳላችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሣዎችንና የምድር አራዊትን፥ የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እግዚአብሔርም አለ፦ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፥ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችንና በአምሳያችን እንፍጠር፤ ሰዎችም በባሕር ውስጥ በሚኖሩ ዓሣዎች፥ በሰማይ በሚበርሩ ወፎች፥ በእንስሶችና በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ በሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች፥ እንዲሁም በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም አለ፤ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን እንስሳትንና ምድርን ሁ፤ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። |
እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ደግሞ ከምድር ፈጠረ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደጠራው ስሙ ያው ሆነ።
እግዚአብሔር አምላክም አለ፥ “እነሆ፥ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፥”
እግዚአብሔር በጊዜው ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፥ እነርሱ ግን ብዙ ዕውቀትን ይሻሉ።
ሰማይን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
የጌታንም ድምፅ፥ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል?” ሲል ሰማሁ? እኔም፥ “እነሆኝ፥ ጌታዬ፥ እኔን ላከኝ” አልሁ።
አሁንም ምድርን ሁሉ ለባሪያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ ያገለግሉትም ዘንድ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አለው፥ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም መጥተን በእርሱ ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን።
እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው።
ወንድ በሚጸልይበት ጊዜ ሊከናነብ አይገባውም፤ የእግዚአብሔር አርአያውና አምሳሉ ነውና፤ ሴትም ለባልዋ ክብር ናት።
እኛስ ሁላችን ፊታችንን ገልጠን በመስተዋት እንደሚያይ የእግዚአብሔርን ክብር እናያለን፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ተሰጠን መጠን የእርሱን አርአያ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንገባለን።
እግዚአብሔርን የሚመስለው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ ልባቸውን አሳውሮአልና።