ዮሐንስ 1:45 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፥ “ሙሴ በሕግ መጽሐፍ፥ ነቢያትም በትንቢት መጻሕፍት ስለ እርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤ እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” አለው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል፤” አለው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ፊልጶስ ግን ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። |
በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በአንተ ዘርና በእርስዋ ዘር መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ። የእርስዋ ዘር የአንተን ራስ ይቀጠቅጣል፤ አንተም የእርስዋን ዘር ተረከዝ ትነክሳለህ።”
‘ሴሎ’ ተብሎ የሚጠራው፥ ሕዝቦች ሁሉ የሚታዘዙለትና ለዘለዓለም የሚነግሠው እስኪመጣ ድረስ፥ በትረ መንግሥት (የገዢነት ሥልጣን) ከይሁዳ እጅ አይወጣም።
በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በምድሪቱ ያለውን የተክልና የዛፍ ቅርንጫፍ ልምላሜ የተዋበና የተከበረ ያደርገዋል፤ ከእስራኤል ወገን ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ምድሪቱ በምታስገኘው ሰብል ደስታና ኲራት ይሰማቸዋል።
አገልጋዬ በደረቅ ምድር ላይ እንደሚወጣ ሥርና እንደ ቡቃያ አድጓል፤ እንመለከተው ዘንድ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤ እርሱን እንወደው ዘንድ ከመልኩ አንዳች እንኳ የሚስብ ደም ግባት የለውም።
እነሆ ሕፃን ተወልዶልናል! ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል! እርሱም መሪ ይሆናል፤ ስሙም “ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ” ይባላል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አንቺ በኤፍራታ ምድር የምትገኚ ቤተልሔም ሆይ! ከይሁዳ ትናንሽ ከተሞች አንድ ብትሆኚም እንኳ ከአንቺ አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ የእስራኤልን ሕዝብ የሚመራ ገዢ ይወጣልኛል።”
የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፦ ‘ቅርንጫፉ በቦታው ስለሚስፋፋ ቅርንጫፍ የሚባል ስም ያለው ይህ ሰው ነው። ባለበት ስፍራ በቅሎ ገናና ይሆናል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ እንደገና ይሠራል፤
ጽዮን ሆይ! ደስ ይበልሽ! ኢየሩሳሌም ሆይ! በደስታ እልል በይ! እነሆ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፥ በአህያይቱ ማለትም በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ፥ በድል አድራጊነት ወደ አንቺ ይመጣል።
ቀጥለውም “ለመሆኑ ይህ እንጨት ጠራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? የያዕቆብ፥ የዮሳ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚህ ከእኛ ጋር አይደሉምን?” እያሉ በመናቅ ሳይቀበሉት ቀሩ።
ዮሴፍም በትውልዱ የዳዊት ዘር ስለ ነበረ በገሊላ ምድር ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ በይሁዳ ምድር ወደምትገኘው ወደ ዳዊት ከተማ፥ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤
ዮሴፍና ማርያም በቤተ መቅደስ ባዩት ጊዜ ተደነቁ፤ በዚያን ጊዜ እናቱ፥ “ልጄ ምነው እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።
ኢየሱስም፥ “ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ የነገርኳችሁ ቃል ይህ ነው” አላቸው።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን ሲጀምር፥ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያኽል ሆኖት ነበር፤ ለሕዝቡ ኢየሱስ የዮሴፍ ልጅ ይመስላቸው ነበር፤ ይኸውም ዮሴፍ የዔሊ ልጅ፥
እንዲህም አሉ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለምን? ታዲያ፥ አሁን እርሱ እንዴት ‘ከሰማይ ወረድኩ’ ይላል?”
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ ቀና ብሎ አየና ፊልጶስን፦ “ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ ከየት መግዛት እንችላለን?” አለው።
“ደግሞም እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ እንደ ቀባውና ኀይልም እንደ ሰጠው ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ እርሱን መልካም ነገርን እያደረገና በዲያብሎስ የተያዙትን ሁሉ እየፈወሰ ተዘዋወረ።
“የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል አዳምጡ፤ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት የናዝሬቱ የኢየሱስ ማንነት እግዚአብሔር በእናንተ መካከል በእርሱ አማካይነት በፈጸማቸው ታላላቅ ሥራዎች፥ ተአምራትና ምልክቶች ተረጋግጦአል።