ዮሐንስ 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ ( ማቴ. 26፥47-56 ፤ ማር. 14፥43-50 ፤ ሉቃ. 22፥47-53 ) 1 ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቄድሮን ሸለቆ ማዶ ሄደ፤ እዚያ ወደነበረውም የአትክልት ቦታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገባ። 2 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እዚያ ቦታ ዘወትር ይሰበሰቡ ስለ ነበር አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ያን ቦታ ያውቅ ነበር። 3 ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ጭፍራ፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩትን የዘብ ኀላፊዎችን አስከትሎ ወደዚያ ቦታ መጣ፤ እነርሱም ፋኖስና ችቦ፥ የጦር መሣሪያም ይዘው ነበር። 4 ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 5 እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም “እኔ ነኝ!” አላቸው። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። 6 ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈገፈጉና በምድር ላይ ወደቁ። 7 ኢየሱስም “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል እንደገና ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉ። 8 እርሱም “እኔ ነኝ ብዬአችኋለሁ፤ እንግዲህ የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ። 9 ይህም የሆነው፥ “አባት ሆይ፥ ከሰጠኸኝ ሰዎች አንዱን እንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። 10 ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፍ ይዞ ስለ ነበረ መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም “ማልኮስ” ይባል ነበር። 11 ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን፥ “ሰይፍህን ወደ አፎቱ ክተተው፤ አብ የሰጠኝን የመከራ ጽዋ የማልጠጣው ይመስልሃልን?” አለው። የኢየሱስ ወደ ሊቀ ካህናቱ መወሰድ 12 ከዚህ በኋላ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድ የዘብ ኀላፊዎችም ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። 13 በመጀመሪያ ወደ ሐና ወሰዱት፤ ሐና በዚያ ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ ዐማቱ ነበር። 14 ቀያፋ “አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት የተሻለ ነው” ሲል የአይሁድ ባለሥልጣኖችን የመከረ ነው። የጴጥሮስ ኢየሱስን መካድ ( ማቴ. 26፥69-70 ፤ ማር. 14፥66-68 ፤ ሉቃ. 22፥55-57 ) 15 ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት፤ ያ ሌላው ደቀ መዝሙር በካህናት አለቃው ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር ወደ ካህናት አለቃው ግቢ ገባ፤ 16 ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ በካህናት አለቃው የታወቀው ደቀ መዝሙር መጣና ለበረኛይቱ ልጃገረድ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው፤ 17 በረኛይቱም ልጃገረድ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ ግን “አይደለሁም” አለ። 18 ጊዜው ብርድ ስለ ነበረ አገልጋዮቹና የዘብ ኀላፊዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ከካህናት አለቃው ለኢየሱስ የቀረበ ጥያቄ ( ማቴ. 26፥59-66 ፤ ማር. 14፥55-64 ፤ ሉቃ. 22፥66-71 ) 19 በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለሰው ሁሉ በግልጥ ተናገርኩ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኲራብም ሆነ በቤተ መቅደስ፥ ዘወትር አስተማርኩ፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም፤ 21 ታዲያ፥ ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገራቸው የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ የተናገርኩትን እነርሱ ያውቃሉ።” 22 ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት የዘብ ኀላፊዎች አንዱ፥ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። 23 ኢየሱስም “ክፉ ቃል ተናግሬ እንደ ሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ የተናገርኩት ትክክል ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። 24 ከዚህ በኋላ ሐና፥ ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ሰደደው። ጴጥሮስ እንደገና ኢየሱስን መካዱ ( ማቴ. 26፥71-75 ፤ ማር. 14፥69-72 ፤ ሉቃ. 22፥58-62 ) 25 የዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ ሌሎች ሰዎችም “አንተስ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” ብሎ ካደ። 26 ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመዱ የሆነው ከካህናት አለቃው ሎሌዎች አንዱ “በአትክልቱ ቦታ ከእነርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው። 27 ጴጥሮስም እንደገና ካደ፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። የኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰድ ( ማቴ. 27፥1-2 ፤ 11-14 ፤ ማር. 15፥1-5 ፤ ሉቃ. 23፥1-5 ) 28 ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ከቀያፋ ቤት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ጊዜውም ጠዋት ማለዳ ነበር፤ አይሁድ ለፋሲካ በዓል የሚታረደውን በግ መብላት ስለ ነበረባቸው እንዳይረክሱ በማለት ወደ አገረ ገዢው ግቢ ውስጥ አልገቡም። 29 ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጣና “በዚህ ሰው ላይ ያቀረባችሁት ክስ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። 30 እነርሱም “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” ሲሉ መለሱለት። 31 ጲላጦስም “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም “እኛ ሰውን ለመግደል አልተፈቀደልንም” አሉት። 32 ይህም የሆነው ኢየሱስ በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። 33 ጲላጦስ እንደገና ወደ ግቢው ተመልሶ ገባ፤ ኢየሱስንም ጠርቶ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው። 34 ኢየሱስ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ይህን ስለ እኔ ነግረውሃል?” አለው። 35 ጲላጦስም “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? አንተን ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ ወገኖችህና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ምንድን ነው ያደረግኸው?” አለው። 36 ኢየሱስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ በአይሁድ ባለሥልጣኖች እጅ እንዳልወድቅ ሎሌዎቼ በተዋጉልኝ ነበር፤ መንግሥቴ ግን ከዚህ ዓለም አይደለችም” ሲል መለሰ። 37 ጲላጦስም “ታዲያ፥ አንተ ንጉሥ ነኻ?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንኩ አንተ ትላለህ፤ እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ልመሰክር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ቃሌን ይሰማል” ሲል መለሰ። 38 ጲላጦስም “እውነት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ እንደገና ወደ አይሁድ ወጣና እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ 39 ነገር ግን እንደ ልማዳችሁ በፋሲካ በዓል ሁልጊዜ አንድ እስረኛ እፈታላችኋለሁ፤ ስለዚህ የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” 40 እነርሱ ግን “በርባንን ፍታልን እንጂ ይህን አይደለም!” እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበር። |