ዮሐንስ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምወደ አብ የሚወስደው መንገድ ኢየሱስ መሆኑ 1 ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ፤ 2 በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ አለበለዚያ ግን ‘የምትኖሩበትን ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ’ ባልኳችሁ ነበር። 3 ሄጄ ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ እኔ ባለሁበት እንድትኖሩ እንደገና መጥቼ እወስዳችኋለሁ። 4 እኔ የምሄድበትንም መንገድ ታውቃላችሁ።” 5 ቶማስ “ጌታ ሆይ! ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፥ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። 6 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7 እኔን ዐውቃችሁኝ ቢሆን ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።” 8 ፊልጶስም “ጌታ ሆይ! አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። 9 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ፊልጶስ ሆይ! ይህን ያኽል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አየ፤ ታዲያ፥ አንተ ‘አብን አሳየን’ እንዴት ትላለህ? 10 እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? ለእናንተ የምናገረውን ቃል የምናገረው በራሴ ሥልጣን አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን ሁሉ የሚሠራው፥ በእኔ የሚኖረው አብ ነው። 11 እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ አለበለዚያ በሥራዎቼ ምክንያት እመኑኝ። 12 እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም ከዚህ የበለጠ ይሠራል፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁ። 13 አብ በወልድ ምክንያት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። 14 ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ተስፋ 15 “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ጠብቁ፤ 16 እኔ አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል። 17 ይህም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም፤ እናንተ ግን፥ እርሱ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነና በውስጣችሁም ስላለ ታውቁታላችሁ። 18 “እናትና አባት እንደሌላቸው ልጆች ብቻችሁን አልተዋችሁም፤ ተመልሼ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ስለ ሆንኩ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ 20 እኔ በአብ እንዳለሁ፥ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ። 21 “እኔን የሚወደኝ ትእዛዜን የሚቀበልና በሥራ ላይ የሚያውለው ነው፤ እኔንም የሚወደኝን አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” 22 አስቆሮታዊው ሳይሆን ሌላው ይሁዳ፥ “ጌታ ሆይ! ራስህን ለዓለም ሳይሆን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። 23 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ እኛ ወደ እርሱ መጥተን ከእርሱ ጋር አብረን እንኖራለን። 24 የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። 25 “አሁን ከእናንተም ጋር እያለሁ ይህን ነገር ነግሬአችኋለሁ፤ 26 አብ በእኔ ስም የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኳችሁንም ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል። 27 “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዐይነት አይደለም፤ ልባችሁ አይጨነቅ፤ ደግሞም አይፍራ። 28 ‘እኔ እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ እንዳልኩ ሰምታችኋል፤ አባቴ ከእኔ ስለሚበልጥ ብትወዱኝስ ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። 29 ይህ በሚሆንበት ጊዜ እንድታምኑ፥ ከመሆኑ በፊት አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። 30 የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን መምጣቱ ስለ ሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም። እርሱ በእኔ ላይ ምንም ኀይል የለውም፤ 31 ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድ ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ተነሡ ከዚህ እንሂድ። |