Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዮሐንስ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢየሱስ ለሰባቱ ደቀ መዛሙርት መገለጥ

1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገለጠ፤ የተገለጠውም እንደሚከተለው ነው፤

2 ስምዖን ጴጥሮስ፥ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፥ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፥ የዘብዴዎስ ልጆችና ሌሎች ሁለት ደቀ መዛሙርት አብረው ነበሩ።

3 ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ለማጥመድ መሄዴ ነው” አላቸው። እነርሱም “ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት፤ ወጥተውም ሄዱና ወደ ጀልባ ገቡ፤ ነገር ግን በዚያች ሌሊት አንድ ዓሣ እንኳ አልያዙም።

4 ሲነጋ ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም።

5 ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች ዓሣ አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የለንም” አሉት።

6 እርሱም “መረቡን ከጀልባው በስተቀኝ በኩል ጣሉና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህ መረቡን በባሕሩ ውስጥ ጣሉት፤ ብዙ ዓሣም ከመያዛቸው የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው።

7 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ ነው እኮ!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስ “ጌታ ነው” ማለትን በሰማ ጊዜ ለሥራ ብሎ ልብሱን አውልቆ ስለ ነበረ ወዲያው ልብሱን ለበሰና ወደ ባሕሩ ዘሎ ገባ።

8 ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት መቶ ሜትር ያኽል ብቻ ስለ ነበረ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።

9 ከጀልባው በወረዱ ጊዜ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ።

10 ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው።

11 ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባው ገብቶ መቶ ኀምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣዎች የሞሉበትን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህን ያኽል ብዙ ዓሣ ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም።

12 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “ኑ ብሉ” አላቸው። ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ሁሉም ዐውቀው ስለ ነበር፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም።

13 ከዚያም ኢየሱስ መጣና፤ እንጀራውንና ዓሣውን አንሥቶ ሰጣቸው።

14 ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ወዲህ ደቀ መዛሙርቱ ሲያዩት ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነበር።


ኢየሱስ ለጴጥሮስ ያቀረበው ጥያቄ

15 ቊርስ ከበሉ በኋላ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! እነዚህ ከሚወዱኝ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት።

16 ኢየሱስም “ግልገሎቼን መግብ” አለው። ሁለተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው።

17 ሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፥ እኔ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “በጎቼን አሰማራ፤

18 እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ቀበቶህን በገዛ እጅህ ታጥቀህ ወደ ፈለግኽበት ትሄድ ነበር፤ በሸመገልክ ጊዜ ግን አንተ እጆችህን ትዘረጋና ሌላ ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማትፈልግበትም ይወስድሃል።”

19 ይህንንም ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ማክበር እንዳለበት ሲያመለክት ነው፤ ከዚህ በኋላ ጴጥሮስን “ተከተለኝ!” አለው።


ኢየሱስና ሌላው ደቀ መዝሙር

20 ጴጥሮስ ዘወር ብሎ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ ይህ ደቀ መዝሙር በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ተጠግቶ፥ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ነው።

21 ጴጥሮስ እርሱን አየና “ጌታ ሆይ! ይህስ ሰው ምን ይሆናል?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀ።

22 ኢየሱስም “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ አንተን ምን አገባህ? አንተ ተከተለኝ!” አለው።

23 በዚህ ምክንያት በወንድሞች መካከል፥ “ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ ተሰራጨ፤ ነገር ግን ኢየሱስ፥ “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ አንተ ምን አገባህ” አለ እንጂ፥ “አይሞትም” አላለም።

24 ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የመሰከረና እነዚህንም ነገሮች የጻፈ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፤ የእርሱም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።

25 ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች ደግሞ አሉ። እኔ እንደሚመስለኝ እርሱ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ አንድ በአንድ ቢጻፉ ኖሮ የሚጻፉትን መጻሕፍት ዓለም ራሱ መሸከም ባልቻለም ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos