Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሉቃስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢየሱስ መፈተን
( ማቴ. 4፥1-11 ፤ ማር. 1፥12-13 )

1 ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ወንዝ ተመለሰ፤ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ በረሓ ሄደ።

2 እዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀኖች ምንም ስላልበላ በመጨረሻ ተራበ።

3 ዲያብሎስም ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ” አለው።

4 ኢየሱስም፦ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት።

5 ከዚህም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ አንድ ከፍተኛ ቦታ ላይ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው።

6 “ይህን ሁሉ ሥልጣንና ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህ ሁሉ ለእኔ የተሰጠኝ ስለ ሆነ ለፈለግሁት መስጠት እችላለሁ፤

7 ስለዚህ አንተ ለእኔ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል፤” አለው።

8 ኢየሱስም፦ “ለጌታ ለአምላክህ ብቻ ስገድ! እርሱንም ብቻ አምልክ! ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት።

9 ከዚያም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ በቤተ መቅደሱም ጣራ ጫፍ ላይ እንዲቆም አድርጎ፥ እንዲህ አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ እስቲ ከዚህ ወደታች ዘለህ ውረድ፤

10 ‘አንተን እንዲጠብቁህ እግዚአብሔር መላእክቱን ያዛል፤

11 እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል፥ በእጃቸው ደግፈው ይይዙሃል፥’ ተብሎ ተጽፎአልና፤” አለው።

12 ኢየሱስም፦ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው፥’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት።

13 ዲያብሎስ ኢየሱስን መፈተኑን ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ትቶት ሄደ።


ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
( ማቴ. 4፥12-17 ፤ ማር. 1፥14-15 )

14 ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተሞልቶ ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አካባቢዎች ሁሉ ተሰማ።

15 በምኲራቦቻቸውም ያስተምር ነበር፤ ሁሉም በትምህርቱ አመሰገኑት።


ኢየሱስ በናዝሬት የደረሰበት ተቃውሞ
( ማቴ. 13፥53-58 ፤ ማር. 6፥1-6 )

16 ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ አደገበት አገር ወደ ናዝሬት ሄደ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኲራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ፤

17 የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ተሰጠው፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፤

18 “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ መልካም ዜናን ለድኾች እንዳበሥር ሾሞኛል፤ ለታሰሩት መፈታትን፥ ለዕውሮች ማየትን እንዳውጅና የተጨቈኑትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል፤

19 እንዲሁም ጌታ ሕዝቡን የሚያድንበትን የጸጋ ዓመት እንዳስታውቅ ልኮኛል።”

20 ኢየሱስ መጽሐፉን አጥፎ ለአስተናባሪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራቡ የነበሩትም ሁሉ ትኲር ብለው ወደ እርሱ ይመለከቱ ጀመር፤

21 እርሱም “እነሆ! ይህ አሁን ሲነበብ የሰማችሁት የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” አላቸው።

22 ስለ እርሱ ሁሉም መልካም ይናገሩ ነበር፤ በሚናገረውም ጸጋን የተመላ ቃል ተደንቀው “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” አሉ።

23 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ ‘አንተ ሐኪም፥ እስቲ ራስህን አድን፥’ የሚለውን ምሳሌ እንደምትጠቅሱብኝ እርግጠኛ ነኝ፤ እንዲሁም ‘በቅፍርናሆም አድርገሃል ሲሉ የሰማነውን ሁሉ፥ እዚህም በገዛ አገርህ አድርግ’ ትሉኛላችሁ።

24 በእውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ ሰዎች ዘንድ አይከበርም።

25 “ስሙኝ እውነቱን ልንገራችሁ፤ በነቢዩ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናም ባለመዝነቡ በአገሩ ሁሉ ብርቱ ራብ ሆኖ ነበር፤ በዚያን ጊዜ በእስራኤል አገር ብዙ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ነበሩ።

26 ነገር ግን ኤልያስ፥ በሲዶና አገር ሰራጵታ በምትባል መንደር ወደምትገኘው ወደ አንዲት ባልዋ የሞተባት ሴት ብቻ ተላከ እንጂ ወደ ሌላ ወደ ማንም አልተላከም።

27 እንዲሁም በነቢዩ በኤልሳዕ ጊዜ ብዙ ለምጻሞች በእስራኤል አገር ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ አልነጻም።”

28 በምኲራብ የነበሩትም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ።

29 ተነሥተውም ኢየሱስን ጐትተው ከከተማ ውጪ አወጡት፤ ወደ ገደልም ገፍትረው ሊጥሉት ፈልገው ከተማቸው ወደ ተሠራችበት ኰረብታ አፋፍ ላይ ወሰዱት።

30 እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።


ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው እንደ ዳነ
( ማር. 1፥21-28 )

31 ከዚህም በኋላ፥ ኢየሱስ በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ከተማ ወደ ቅፍርናሆም ሄደ፤ በዚያም፥ ሕዝቡን በሰንበት ቀን ያስተምር ነበር።

32 በሥልጣን ቃል ይናገር ስለ ነበር ሁሉም በትምህርቱ ይደነቁ ነበር።

33 እዚያም በምኲራብ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ነበር፤ እርሱ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ጮኸ፤

34 “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።”

35 ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ፥ “ዝም ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ሲል ገሠጸው፤ ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን በሕዝቡ ፊት ጣለውና ምንም ሳይጐዳው ወጣ።

36 ሁሉም በመደነቅ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ምን ዐይነት ቃል ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዛል፤ እነርሱም ታዘው ይወጣሉ፤” ተባባሉ።

37 የኢየሱስም ዝና በዚያ አገር ዙሪያ ሁሉ ተሰማ።


ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችን መፈወሱ
( ማቴ. 8፥14-17 ፤ ማር. 1፥29-34 )

38 ኢየሱስ ከምኲራብ ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ሄደ፤ እዚያም የስምዖን ዐማት በጣም አተኲሶአት ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለዚህ እንዲያድናት ኢየሱስን ለመኑት።

39 ኢየሱስም ወደ እርስዋ ቀርቦ አጠገብዋ ቆመና ትኲሳቱ እንዲለቃት አዘዘ፤ ትኲሳቱም ለቀቃት፤ ወዲያውኑም ተነሥታ ታስተናግዳቸው ጀመር።

40 ፀሐይ ስትጠልቅ ሰዎች በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙባቸውን ሕመምተኞች ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን በመጫን ፈወሳቸው።

41 አጋንንትም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ በመጮኽ ብዙ ሰዎችን እየለቀቁ ይወጡ ነበር፤ እርሱ መሲሕ መሆኑንም ዐውቀው ነበር፤ ኢየሱስ ግን ስለ እርሱ ምንም እንዳይናገሩ በመገሠጽ ይከለክላቸው ነበር።


ኢየሱስ በገሊላ ማስተማሩ
( ማቴ. 4፥23-25 ፤ ማር. 1፥35-39 )

42 በነጋም ጊዜ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሰው ወደሌለበት ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሄደ፤ ሰዎቹም ይፈልጉት ነበር፤ ባገኙትም ጊዜ “ተለይተኸን አትሂድብን” ብለው ለመኑት።

43 እርሱ ግን “እኔ የተላክሁት ለዚህ ስለ ሆነ ወደ ሌሎችም ከተሞች ሄጄ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል ማብሠር ይገባኛል፤” አላቸው።

44 ስለዚህ በይሁዳም ምኲራቦች ሁሉ እየተዘዋወረ ይሰብክ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos