ማርቆስ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበኢየሱስ ላይ የተደረገ ሤራ ( ማቴ. 26፥1-5 ፤ ሉቃ. 22፥1-2 ፤ ዮሐ. 11፥45-53 ) 1 የአይሁድ የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ቀርቶት ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስን በተንኰል ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። 2 ነገር ግን ሕዝቡ ሁከት ያነሣሣል በማለት “በበዓል ቀን ይህን አናደርግም፤” አሉ። ኢየሱስን ሽቶ የቀባች ሴት ( ማቴ. 26፥6-13 ፤ ዮሐ. 12፥1-8 ) 3 ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበር። በገበታም ቀርቦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነና የከበረ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት፥ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡን ሰብራ ሽቶውን በኢየሱስ ራስ ላይ አፈሰሰችው። 4 እዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው፦ “ይህ ሽቶ በከንቱ መባከኑ ለምንድን ነው? 5 ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ሊሰጥ ይቻል ነበር!” ተባባሉ፤ ሴቲቱንም ነቀፉአት። 6 ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “ተዉአት! ስለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ 7 ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ስለ ሆኑ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዱአቸው ትችላላችሁ፤ እኔን ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አታገኙኝም፤ 8 ይህች ሴት የተቻላትን አድርጋለች፤ ሥጋዬም ከመቀበሩ በፊት አስቀድማ ለማዘጋጀት ሽቶ ቀባችው። 9 በእውነት እላችኋለሁ፤ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያ ይነገርላታል።” ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱ ( ማቴ. 26፥14-16 ፤ ሉቃ. 22፥3-6 ) 10 ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ አስቆሮታዊው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 11 እነርሱም ይህን ባወቁ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ቃል ገቡለት። እርሱም ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ኢየሱስ የአይሁድን የፋሲካ ራት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ በላ ( ማቴ. 26፥17-25 ፤ ሉቃ. 22፥7-14 ፤ 21-23 ፤ ዮሐ. 13፥21-30 ) 12 የፋሲካውን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “የፋሲካን ራት ለመብላት ወዴት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። 13 እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እዚያም የውሃ እንሥራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከተሉት፤ 14 ወደሚገባበትም ቤት ሂዱና የቤቱን ጌታ፥ ‘መምህር፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት ለእኔ የሚሆን የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው?’ ይላል በሉት። 15 እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን የተዘጋጀውንና የተነጠፈውን ትልቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” 16 ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከዚያ ወጥተው ወደ ከተማው ሄዱ፤ ልክ ኢየሱስ እንዳላቸውም አገኙ፤ የፋሲካንም ራት በዚያ አዘጋጁ። 17 በመሸ ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ፤ 18 በገበታ ቀርበው ሲበሉ ኢየሱስ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል፤ እርሱም አሁን ከእኔ ጋር ራት በመብላት ላይ የሚገኘው ነው፤” አለ። 19 እነርሱም በዚህ ነገር አዝነው “እኔ እሆንን?” እያሉ ተራ በተራ ጠየቁት። 20 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ያ ሰው ከዐሥራ ሁለታችሁ አንዱ የሆነው አሁን ከእኔ ጋር በዚህ ሳሕን ውስጥ ወጥ የሚያጠቅሰው ነው፤ 21 የሰው ልጅ አስቀድሞ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ወደ ሞት መሄዱ አይቀርም፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰውስ ቀድሞውኑ ባይወለድ ይሻለው ነበር!” የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት ( ማቴ. 26፥26-30 ፤ ሉቃ. 22፥14-20 ፤ 1ቆሮ. 11፥23-25 ) 22 እነርሱ በመብላት ላይ ሳሉ ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፥ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። 23 ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከጽዋው ጠጡ። 24 እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የቃል ኪዳን ደሜ ነው፤ 25 በእውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከአዲሱ ወይን እስክጠጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም።” 26 ከዚያም በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ተናገረ ( ማቴ. 26፥31-35 ፤ ሉቃ. 22፥31-34 ፤ ዮሐ. 13፥36-38 ) 27 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ ‘እረኛውን መትቼ እገድላለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ፤’ ተብሎ ተጽፎአልና ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ፤ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ትታችሁኝም ትሸሻላችሁ፤ 28 ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” 29 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ፥ እኔ ከቶ አልክድህም!” አለው። 30 ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። 31 ጴጥሮስ ግን “መሞት እንኳ ቢያስፈልግ ከአንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” እያለ አጠንክሮ ተናገረ። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት እንዲሁ ይሉ ነበር። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ እንደ ጸለየ ( ማቴ. 26፥36-46 ፤ ሉቃ. 22፥39-46 ) 32 ከዚህም በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ፤” አላቸው። 33 ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም አስከትሎ ሄደ፤ እዚያም እጅግ ያዝንና ይጨነቅ ጀመረ። 34 እንዲህም አላቸው፦ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዝናለች፤ እዚህ ቈዩ፤ ተግታችሁም ጠብቁ።” 35 ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደ፤ በመሬትም ላይ በግንባሩ ተደፍቶ የሚቻል ቢሆን ያቺ ሰዓት እንድታልፍለት ጸለየ። 36 እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፥ ሁሉ ነገር ይቻልሃል፤ ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ ፈቃድ አይሁን።” 37 ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ ጴጥሮስን፦ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት እንኳ ልትነቃ አልቻልክምን?” አለው። 38 “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አላቸው። 39 እንደገናም ሄዶ፥ ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ጸለየ። 40 ደግሞም ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር፥ ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። 41 ሦስተኛም ጊዜ ወደ እነርሱ መጥቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን? እንግዲህስ በቃ! ሰዓቱ ደርሶአል! እነሆ! የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። 42 በሉ ተነሡ! እንሂድ! አሳልፎ የሚሰጠኝ ይኸው ቀርቦአል!” የኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ ( ማቴ. 26፥47-56 ፤ ሉቃ. 22፥47-53 ፤ ዮሐ. 18፥3-12 ) 43 ወዲያውም ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ የተላኩ ነበሩ። 44 አሳልፎ የሚሰጠውም ይሁዳ፥ “እናንተ የምትይዙት እኔ ሰላምታ ሰጥቼ የምስመውን ነው፤ እርሱን በጥንቃቄ ይዛችሁ ውሰዱት፤” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 45 ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው። 46 ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ያዙት። 47 እዚያ ቆመው ከነበሩት ከኢየሱስ ተከታዮች አንዱ ሰይፉን መዝዞ የካህናት አለቃውን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ። 48 ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን እንደ ወንበዴ ለመያዝ ነውን? 49 በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ የሆነው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዲፈጸም ነው።” 50 ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ትተውት ሸሹ። 51 የበፍታ ነጠላ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት ግን ኢየሱስን ይከተል ነበር፤ ሰዎቹም በያዙት ጊዜ 52 ነጠላውን ጥሎ ራቁቱን ሸሽቶ አመለጠ። ኢየሱስ ወደ ፍርድ ሸንጎ መወሰዱ ( ማቴ. 26፥57-68 ፤ ሉቃ. 22፥54-55 ፤ 63-71 ፤ ዮሐ. 18፥13-14 ፤ 19-24 ) 53 ኢየሱስን ግን ወደ ካህናት አለቃው ቤት ወሰዱት፤ እዚያ የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሕግ መምህራን ሁሉ ተሰበሰቡ። 54 ጴጥሮስም እስከ የካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ይከተለው ነበር። እዚያም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። 55 የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች ሁሉ፥ ኢየሱስን ለማስገደል ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ግን አላገኙም። 56 ብዙዎችም በሐሰት መስክረውበት ነበር፤ ሆኖም የምስክርነት ቃላቸው ሳይስማማ ቀረ። 57 አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ 58 “እኔ ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ሌላ በሰው እጅ ያልተሠራ እሠራለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” 59 ይህም ሆኖ ምስክርነታቸው አልተስማማም። 60 የካህናት አለቃውም በመካከላቸው ቆሞ፥ “ምንም አትመልስምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚያቀርቡብህ ክስ ምንድን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። 61 ኢየሱስ ግን ዝም አለ እንጂ ምንም መልስ አልሰጠም። የካህናት አለቃውም “የቡሩክ እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ አንተ ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው። 62 ኢየሱስም “አዎ፥ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታያላችሁ! እንዲሁም በሰማይ ደመና ተመልሶ ሲመጣ ታያላችሁ” አለ። 63 የካህናት አለቃውም በቊጣ ልብሱን ቀደደና “ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? 64 እነሆ! ይህን የስድብ ቃል በእግዚአብሔር ላይ ሲሰነዝር ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” አለ። ሁሉም በአንድ ቃል፥ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። 65 አንዳንዶችም ምራቃቸውን እንትፍ ይሉበት ጀመር፤ ዐይኑንም በጨርቅ ሸፍነው “አንተ ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደ መታህ ዕወቅ!” እያሉ በቡጢ ይመቱት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ ኢየሱስን መካዱ ( ማቴ. 26፥69-75 ፤ ሉቃ. 22፥56-62 ፤ ዮሐ. 18፥15-18 ፤ 25-27 ) 66 ጴጥሮስ ከካህናት አለቃው ቤት በታች በግቢው ውስጥ እንዳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንድዋ መጣች፤ 67 እርስዋ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኲር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ፤” አለችው። 68 እርሱ ግን “እኔ አላውቅም፤ አንቺ የምትዪውም አይገባኝም፤” ሲል ካደ። ይህንንም ብሎ ወደ ደጃፉ እንደ ወጣ ዶሮ ጮኸ። 69 ገረዲትዋም ጴጥሮስን አይታ፥ በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው!” ስትል እንደገና ትናገር ጀመር፤ 70 እርሱ ግን እንደገና ካደ። ጥቂት ቈየት ብሎም በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው መሆንህን በእርግጥ አነጋገርህ ያስረዳል፤ ስለዚህ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤” አሉት። 71 እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ። 72 ወዲያውኑ ዶሮ ሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለውና ምርር ብሎ አለቀሰ። |