ኢሳይያስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 በዚያን ጊዜ ሰባት ሴቶች አንዱን ወንድ ይዘው “በምግብም ሆነ በልብስ ራሳችንን ችለን እንተዳደራለን፤ ‘ባል የላቸውም’ ተብለን ከመሰደብ እንድንድን የአንተ ሚስቶች ተብለን እንድንጠራ ብቻ ፍቀድልን” ብለው ይለምኑታል። የኢየሩሳሌም እንደገና መታደስ 2 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በምድሪቱ ያለውን የተክልና የዛፍ ቅርንጫፍ ልምላሜ የተዋበና የተከበረ ያደርገዋል፤ ከእስራኤል ወገን ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ምድሪቱ በምታስገኘው ሰብል ደስታና ኲራት ይሰማቸዋል። 3 በኢየሩሳሌም የተረፉትና በኢየሩሳሌምም እንዲኖሩ የተፈቀደላቸው ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ። 4 የኢየሩሳሌምን ርኲሰት ያጠራል፤ በፍርዱና በመንፈሱ ኀይል ደም አፍሳሽነትን ከመኻልዋ ያስወግዳል። 5 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር መላውን ከተማና በእዚያም በሚሰበሰቡበት ሁሉ ላይ በቀን ጥቅጥቅ ያለ ደመናን፥ በየሌሊቱም በሚንበለበለው የእሳት ብርሃን ይልካል። የእግዚአብሔርም ክብር ከተማይቱን እንደ ትልቅ ድንኳን ሸፍኖ ይጠብቃታል። 6 የእርሱ ክብር ከተማይቱን ከቀኑ የፀሐይ ቃጠሎ ይጋርዳታል፤ ከዝናብና ከዐውሎ ነፋስ መጠጊያና መሸሸጊያ ስፍራ ይሆናታል። |