ዘፍጥረት 1:14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ቀንን ከሌሊት ለመለየት ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ላይ ይሁኑ፤ ለዕለታት፥ ለክፍላተ ዓመትና ለዓመታት መለያ ምልክት ይሁኑ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እግዚአብሔርም አለ፦ “ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፥ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፥ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም አለ፥ “በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ፥ በቀንና በሌሊትም ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች፥ ለዘመናት፥ ለዕለታት፥ ለዓመታትም ይሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም አለ፤ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤ |
ቀና ብላችሁ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ የምታዩአቸውን ከዋክብት የፈጠረ ማን ነው? እርሱ እንደ ጦር ሠራዊት ይመራቸዋል፤ ምን ያኽል እንደ ሆኑም ቊጥራቸውን ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል፤ የእርሱ ሥልጣንና ኀይል እጅግ ታላቅ ነው፤ ስለዚህ ከእነርሱ አንዱ እንኳ አይጠፋም።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የአሕዛብን አካሄድ አትከተሉ፤ መቼም አሕዛብ ያልተለመደ አዲስ ነገር በሰማይ ባዩ ጊዜ በፍርሃት መንቀጥቀጥ ልማዳቸው ነው፤ እናንተ ግን በዚህ አትሸበሩ።
ፀሐይን በቀን እንዲያበራ የሚያደርገው፥ ጨረቃና ከዋክብት በሌሊት እንዲያበሩ ሥርዓትን የወሰነላቸው፥ ባሕሩን በማዕበል እንዲናወጥ የሚቀሰቅሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ስሙም የሠራዊት አምላክ ነው።
“ለአገልጋዬ ለዳዊት ዙፋን የሚወርስ ልጅ እንደምሰጠው የገባሁት ቃል ኪዳንና ለአገልጋዮቼ ለሌዋውያን ስለሚሰጡኝ አገልግሎት ያቆምኩላቸው ቃል ኪዳን ሊፈርሱ የሚችሉት ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዲመጡ ያቆምኩላቸውን ሥርዓት ከእናንተ መካከል ለማፍረስ የሚችል ሰው የተገኘ ከሆነው ነው።
ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባው ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚያመለክተው በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ዝግ መሆን አለበት፤ ነገር ግን በሰንበት ቀንና በየወሩ መባቻ ቀን ይከፈታል።
“ፕሊያዲስ” የተባሉትን ሰባቱን ከዋክብትና “ኦርዮን” ተብለው የሚጠሩትን የከዋክብት ክምችትን የፈጠረ፥ ሌሊቱን ወደ ቀን፥ ቀኑንም ወደ ሌሊት የሚለውጥ፥ የባሕሩን ውሃ አዞ፥ በምድር ላይ እንዲፈስ የሚያደርግ፥ ኀያላንንና ምሽጎቻቸውን የሚደመስስ እርሱ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው።
“ከነዚያ ከመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይሎችም ይናወጣሉ።
በሰማይ ላይ የምታዩአቸውን ፀሐይንና ጨረቃን ወይም ከዋክብትን ወይም የሰማይን ሠራዊት ሁሉ በማምለክና ለእነርሱ በመስገድ እንዳትፈተኑ ተጠንቀቁ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ እነዚህን ሁሉ ሌሎች ሕዝቦች ብቻ ያመልኩአቸው ዘንድ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል።
ከዚህ በኋላ በጉ ስድስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለከትኩ፤ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሐይ እንደ ጥቊር የሐዘን ልብስ ጠቈረች፤ ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች፤
አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ አንድ ሦስተኛ፥ የጨረቃ አንድ ሦስተኛ፥ የኮከቦች አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ ስለዚህ የእነርሱ አንድ ሦስተኛቸው ጨለመ፤ በዚህ ዐይነት የቀን አንድ ሦስተኛና የሌሊት አንድ ሦስተኛ ያለ ብርሃን ሆነ።
እርሱ የጥልቁን ጒድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጥልቁ ጒድጓድ ወጣ፤ ከጒድጓዱ በወጣው ጢስ ምክንያት ፀሐይና አየር ጨለሙ፤