Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሉቃስ 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰዱ
( ማቴ. 27፥1-2 ፤ 11-14 ፤ ማር. 15፥1-5 ፤ ዮሐ. 18፥28-38 )

1 በዚያ ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች ሁሉ ተነሥተው ኢየሱስን ወሰዱትና በጲላጦስ ፊት አቀረቡት፤

2 እንዲህ እያሉም ይከሱት ጀመር፤ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያስት አገኘነው፤ ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር እንዳይከፈል ይከለክላል፤ ደግሞ ‘እኔ ንጉሥ መሲሕ ነኝ’ እያለ ይናገራል።”

3 ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው” አለው።

4 በዚያን ጊዜ ጲላጦስ ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡም “በዚህ ሰው ምንም በደል አላገኘሁበትም” አለ።

5 እነርሱ ግን “ይህ ሰው ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ለሁከት ያነሣሣል” እያሉ በጥብቅ ከሰሱት።


ኢየሱስ በሄሮድስ ፊት መቅረቡ

6 ጲላጦስም ገሊላ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፥ “ይህ የገሊላ ሰው ነውን?” ብሎ ጠየቀ።

7 ኢየሱስ የመጣው ከሄሮድስ ግዛት መሆኑን ጲላጦስ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ላከው፤ ሄሮድስም በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበር።

8 ሄሮድስ ኢየሱስን ባየ ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ ኢየሱስ ይሰማ ነበርና ሊያየው ብዙ ጊዜ ይመኝ ነበር፤ እንዲሁም ኢየሱስ ተአምር ሲያደርግ ለማየት ተስፋ ያደርግ ነበር።

9 ስለዚህ ሄሮድስ ኢየሱስን ብዙ ጥያቄ ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም።

10 የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን እዚያ ቆመው በብርቱ ይከሱት ነበር።

11 ሄሮድስም ከጭፍሮቹ ጋር ሆኖ በንቀት አፌዘበት፤ ጌጠኛ ልብስ አልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ላከው።

12 በዚያን ቀን ሄሮድስና ጲላጦስ ወዳጆች ሆኑ፤ ከዚያ በፊት ግን ጠበኞች ነበሩ።


ኢየሱስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት
( ማቴ. 27፥15-26 ፤ ማር. 15፥6-15 ፤ ዮሐ. 18፥39-40 ፤ 19፥1-16 )

13 ከዚህ በኋላ ጲላጦስ የካህናት አለቆችን፥ የሕዝብ መሪዎችንና ሕዝቡንም ጭምር በአንድነት ጠራ፤

14 እንዲህም አላቸው፤ “ ‘ሕዝቡን ለሁከት ያነሣሣል’ ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እኔም እነሆ፥ በፊታችሁ መርምሬው ካቀረባችሁበት ክስ ሁሉ በዚህ ሰው ላይ ምንም በደል አላገኘሁበትም።

15 እንዲሁም ሄሮድስ ምንም በደል ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶ ልኮታል፤ እንግዲህ ይህ ሰው ለሞት የሚያደርሰው ምንም ነገር አላደረገም።

16 ስለዚህ ገርፌ እለቀዋለሁ።”

17 [በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ጲላጦስ አንድ እስረኛ ለሕዝቡ ይፈታላቸው ነበር]

18 ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ “ይህን ሰው አስወግደው! በርባንን ግን ፍታልን!” እያሉ በአንድ ድምፅ ጮኹ።

19 በርባን በከተማ ውስጥ ብጥብጥ በማስነሣትና ሰውን በመግደል ምክንያት በወህኒ ቤት የታሰረ ሰው ነበር።

20 ጲላጦስ ኢየሱስን ፈቶ ሊለቀው ፈልጎ እንደገና ለሕዝቡ ተናገረ።

21 ሕዝቡ ግን “ስቀለው! ስቀለው!” እያለ ጮኸ።

22 ጲላጦስም ሦስተኛ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ሰው ያደረገው በደል ከቶ ምንድን ነው? እኔ ለሞት የሚያደርስ ምንም ነገር አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ገርፌ እለቀዋለሁ።”

23 እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ፤ የሕዝቡና የካህናት አለቆች ድምፅ አየለ።

24 በዚህም ምክንያት የጠየቁት እንዲደረግላቸው ጲላጦስ ፈረደ።

25 ብጥብጥ በማስነሣትና ሰው በመግደል ታስሮ የነበረውን በርባንን በጥያቄአቸው መሠረት ለቀቀው፤ ኢየሱስን ግን እንደ ፍላጎታቸው አሳልፎ ሰጣቸው።


የኢየሱስ መሰቀል
( ማቴ. 27፥32-44 ፤ ማር. 15፥21-32 ፤ ዮሐ. 19፥17-27 )

26 ስለዚህ ኢየሱስን ወሰዱት፤ ይዘውት ሲሄዱ ሳሉም የቀሬና ሰው የሆነውን ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ እርሱን ይዘው የኢየሱስን መስቀል አሸከሙትና ኢየሱስን እንዲከተል አደረጉት።

27 ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ።

28 ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ!

29 ‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ።

30 በዚያን ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን፥ ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም፥ ‘ሸሽጉን!’ ማለት ይጀምራሉ።

31 እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?”

32 እንዲሁም ሁለት ወንጀለኞችን ከኢየሱስ ጋር ሊገድሉአቸው ይዘው ሄዱ።

33 ቀራንዮ ወይም የራስ ቅል ወደ ተባለ ስፍራም በደረሱ ጊዜ በዚያ ኢየሱስን ሰቀሉት፤ እንዲሁም ሁለቱን ወንጀለኞች በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሰቀሉአቸው።

34 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” አለ። ወታደሮቹም ዕጣ ተጣጥለው የኢየሱስን ልብስ ተከፋፈሉ።

35 ሕዝቡ ቆሞ ይመለከት ነበር፤ የአይሁድ አለቆችም “ሌሎችንስ አዳነ እንግዲህ እርሱ የተመረጠው የእግዚአብሔር መሲሕ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር።

36 ወታደሮቹም እንዲሁ አፌዙበት፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ ሰጡት።

37 እንዲሁም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ እስቲ ራስህን አድን!” ይሉት ነበር።

38 “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍም በኢየሱስ ራስጌ በመስቀሉ ላይ አኖሩ።


ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉት ሁለት ወንጀለኞች
( ማቴ. 27፥38-44 ፤ ማር. 15፥27-32 )

39 ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ፥ ኢየሱስን፦ “አንተ መሲሕ አይደለህምን? እስቲ በል ራስህንና እኛን አድን!” እያለ ይሰድበው ነበር።

40 ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ብሎ ገሠጸው፦ “አንተ በተመሳሳይ ፍርድ ላይ እያለህ እግዚአብሔርን አትፈራምን?

41 እኛ ባደረግነው በደል ምክንያት የሚገባንን ቅጣት አግኝተናል፤ ይህ ሰው ግን ምንም ጥፋት አላደረገም።”

42 ቀጥሎም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስታውሰኝ!” አለው።

43 ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” አለው።


የኢየሱስ ሞት
( ማቴ. 27፥45-56 ፤ ማር. 15፥33-41 ፤ ዮሐ. 19፥28-30 )

44 እነሆ፥ ይህ የሆነው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።

45 ፀሐይ ጨለመ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከመካከሉ ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ።

46 ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ! እነሆ! ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ!” አለ፤ ይህንንም ካለ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች።

47 በዚያ የነበረው መቶ አለቃ፥ የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ሰው ጻድቅ ኖሮአል!” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ።

48 ነገሩን ለመመልከት እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በማዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደየቤታቸው ተመለሱ።

49 ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩ ሴቶችም በሩቅ ቆመው ይህን ነገር ይመለከቱ ነበር።


የኢየሱስ መቀበር
( ማቴ. 27፥57-61 ፤ ማር. 15፥42-47 ፤ ዮሐ. 19፥38-42 )

50 የአይሁድ ከተማ በሆነችው በአርማትያስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱ ጻድቅና ደግ ሰው ነበረ፤ የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበረ።

51 ይሁን እንጂ በአይሁድ ምክርና ሤራ አልተባበረም፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበረ።

52 ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ።

53 አስከሬኑንም አውርዶ በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ሰው ባልተቀበረበት ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤

54 ይህንንም ያደረገው ዓርብ ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነበር።

55 ኢየሱስን ተከትለው ከገሊላ የመጡ ሴቶች ከዮሴፍ ጋር ሄደው መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንደ ተቀበረ ተመለከቱ።

56 ወደ ቤታቸውም ተመልሰው ለአስከሬን የሚሆኑ ጥሩ መዓዛ ያለው ቅመምና ሽቶ አዘጋጁ፤ በሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ዐርፈው ዋሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos