ማርቆስ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሰለ ቤተ መቅደስ መፍረስ የኢየሱስ ትንቢት ( ማቴ. 24፥1-2 ፤ ሉቃ. 21፥5-6 ) 1 ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “መምህር ሆይ! እነዚህን ድንጋዮችና ሕንጻዎች ተመልከት፤ የሚያስደንቁ ናቸው!” 2 ኢየሱስም “እነዚህን ትልልቅ ሕንጻዎች ታያለህን? እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የሚቀር የለም፤” ብሎ መለሰለት። የዘመኑ መጨረሻ ምልክቶች ( ማቴ. 24፥3-14 ፤ ሉቃ. 21፥7-19 ) 3 ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስና፥ እንድርያስ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው 4 “ይህ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ ሁሉ ሊፈጸም ሲቃረብ ምልክቱ ምንድን ነው? እስቲ ንገረን” ሲሉ ጠየቁት። 5 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤ 6 ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ፤ 7 በአቅራቢያችሁ ጦርነት ሲደረግና በሩቅም የጦርነትን ወሬ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ ሁሉ ሊሆን ግድ ነው፤ ይሁን እንጂ መጨረሻው ገና ነው። 8 ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ጦርነት ያነሣል፤ በየስፍራው የምድር መናወጥና ራብ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ነው። 9 “እናንተም ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በየምኲራቡም ይገርፉአችኋል፤ ምስክር እንድትሆኑኝ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ለፍርድ ትቆማላችሁ። 10 ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ወንጌል ለዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳረስ ይገባዋል። 11 ሰዎች ይዘው ወደ ፍርድ ሲያቀርቡአችሁ፥ ‘ምን እንናገር ይሆን?’ በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም። ስለዚህ በዚያን ሰዓት የሚሰጣችሁን ብቻ ተናገሩ። 12 ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም። 13 ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። አሠቃቂው መከራ ( ማቴ. 24፥15-28 ፤ ሉቃ. 21፥20-24 ) 14 “ደግሞ መገኘት በማይገባው ስፍራ የሚያረክሰውን አጸያፊ ነገር ታያላችሁ፤ ይህንንም አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ምድር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ። 15 በቤት ጣራ ላይ ያለ ወደ ቤቱ ወርዶ ከቤቱ አንዳች ነገር ለመውሰድ ጊዜ አያጥፋ፤ 16 በእርሻም ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ ወደ ኋላው አይመለስ። 17 በዚያን ጊዜ ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! 18 ይህ ሁሉ በክረምት ጊዜ እንዳይሆን ጸልዩ። 19 በዚያን ወራት እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ መከራ ይሆናል፤ ወደ ፊትም እሱን የሚመስል ጭንቀት ከቶ አይደርስም። 20 ጌታ እነዚያን ቀኖች ባያሳጥርማ ኖሮ ማንም መዳን ባልቻለም ነበር፤ ነገር ግን ለተመረጡት ሰዎች ሲባል እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። 21 “እንግዲህ ማንም ቢሆን ‘መሲሕ ይኸው እዚህ ነው!’ ወይም ‘ያው እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። 22 ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይመጣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳሳት ተአምራትና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋሉ። 23 ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁና እንግዲህ ተጠንቀቁ! የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ( ማቴ. 24፥29-31 ፤ ሉቃ. 21፥25-28 ) 24 “በዚያን ጊዜ፥ ከዚያ ሁሉ መከራ በኋላ፥ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ 25 ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማይ ያሉ ኀይሎችም ይናወጣሉ። 26 ከዚያም በኋላ የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ይታያል፤ 27 መላእክቱንም ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም አቅጣጫ ሄደው ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የሚገኙትን፥ ለእርሱ የተመረጡትን ሰዎች ይሰበስባሉ። የጌታን መምጫ የምታመለክት የበለስ ዛፍ ምሳሌ ( ማቴ. 24፥32-35 ፤ ሉቃ. 21፥29-33 ) 28 “የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። 29 እንዲሁም እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ፤ 30 በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ከማለፉ በፊት ይህ ሁሉ ይፈጸማል። 31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ጸንቶ ይኖራል። ጌታ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ማንም አያውቅም ( ማቴ. 24፥36-44 ) 32 “ነገር ግን ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ የሰማይ መላእክትም አያውቁም፤ ወልድም አያውቅም። 33 ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ። 34 ይህም፥ ቤቱን ትቶ ወደ ሩቅ አገር የሄደውን ሰው ይመስላል፤ እርሱም እያንዳንዱን አገልጋይ በልዩ ልዩ የሥራ ኀላፊነት ላይ መደበ፤ ዘበኛውንም ተግቶ እንዲጠብቅ አዘዘው። 35 ስለዚህ የቤቱ ጌታ የሚመጣበትን ጊዜ አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ምናልባትም ወደ ማታ፥ ወይም በእኩለ ሌሊት፥ ወይም ዶሮ ሲጮኽ፥ ወይም ጠዋት በማለዳ ይመጣ ይሆናል፤ 36 በድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ትጉ። 37 “ለእናንተ እንደ ነገርኳችሁ ለሌሎችም ሁሉ ትጉ! እላለሁ።” |