Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


አሞጽ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


አሞጽ የጐመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት በራእይ ማየቱ

1 ጌታ እግዚአብሔር ሌላ ራእይ ገለጠልኝ፤ እነሆ የጐመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት አየሁ፤

2 እግዚአብሔርም “ይህ የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “የጐመራ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት አያለሁ” አልኩት። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ “የሕዝቤ የእስራኤል ፍጻሜ ደርሶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ እነርሱን ከመቅጣት አልመለስም።

3 በቤተ መንግሥት የሚያሰሙት ዘፈን በዚያን ቀን ወደ ለቅሶ ይለወጣል፤ የብዙ ሰው ሬሳ በየቦታው ወድቆ ይገኛል፤ በዝምታም በየስፍራው ይጣላል።”


የእስራኤል ውድቀት

4 እናንተ የችግረኞችን መብት የምትረግጡና ድኾችን ከአገር ለማጥፋት የምትፈልጉ ሁሉ! ይህን ስሙ!

5 እናንተ እንዲህ ትላላችሁ፦ “እህላችንን መሸጥ እንድንችል የወር መባቻው በዓል ምነው ቶሎ ባለፈልን! ስንዴ ወደ ገበያ ለመውሰድ ሰንበትም መቼ ያልፍልናል? በዓላቱ ካለፉልን የእህሉን መስፈሪያ አሳንሰን ከፍተኛ ዋጋ እንጠይቃለን፤ በሐሰተኛ ሚዛንም ሕዝቡን እናታልላለን፤

6 የስንዴውን ግርድ እንኳ እንሸጣለን፤ ድኻውን በብር ችግረኛውንም በአንድ ጥንድ ነጠላ ጫማ እንገዛለን።”

7 ለያዕቆብና ለዘሮቹ መመኪያ የሆነው እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ማለ፦ “እነርሱ የሠሩትን ሥራ ሁሉ አልረሳም።

8 በዚህ ነገር ምድር ትናወጣለች፤ በአገሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የዓባይ ወንዝ ሞልቶ በመጒደል እንደሚናወጥ አገሪቱ በሞላ ትናወጣለች።”

9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ገና በእኩለ ቀን ፀሐይ እንድትጠልቅ አደርጋለሁ፤ በቀትርም ምድሪቱን አጨልማለሁ።

10 የዓመት በዓል ደስታችሁን ወደ ሐዘን፥ ዘፈናችሁንም ወደ ለቅሶ እለውጠዋለሁ፤ አንድ ብቻ የሆነ ልጃቸው ሞቶባቸው እንደሚያለቅሱ ወላጆች ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ ማቅ እንድትለብሱ አደርጋለሁ፤ የዚያ ቀን ፍጻሜ የመረረ ይሆናል።

11 “እነሆ በምድር ላይ ራብን የማመጣበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜም ሰዎች የሚራቡትና የሚጠሙት የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ነው እንጂ ምግብና ውሃ በማጣት አይደለም፤ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

12 ሕዝቡ ሁሉ ከሰሜን እስከ ደቡብ፥ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የእግዚአብሔርንም ቃል ለማግኘት በሁሉ ቦታ ይንከራተታሉ፤ ነገር ግን አያገኙም።

13 በዚያን ጊዜ ቆነጃጅት ልጃገረዶችና ጠንካራ ወንዶች ወጣቶች እንኳ ከመጠማት የተነሣ ይዝላሉ፤

14 ‘አሺማ’ ተብላ በምትጠራ በሰማርያ ሴት አምላክ የሚምሉ ‘በዳን አምላክ’ ወይም ‘በቤርሳቤህ አምላክ’ እያሉ የሚምሉ ሁሉ ይወድቃሉ፤ ከወደቁበትም ፈጽሞ መነሣት አይችሉም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos