መዝሙር 81 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየክብረ በዓል መዝሙር 1 ለመከታችን ለእግዚአብሔር በደስታ ዘምሩ! ለያዕቆብ አምላክ እልል በሉ! 2 መዝሙር ለመዘመር ተነሡ፤ ከበሮም ምቱ፤ በበገናና በመሰንቆ ደስ የሚያሰኝ ዜማ አሰሙ። 3 ለበዓሉ ክብር መለከት ንፉ፤ አዲስ ጨረቃ ስትወጣና ሙሉ ጨረቃ ስትሆን ይህንኑ አድርጉ። 4 ይህ ለእስራኤል የተደነገገ፥ የያዕቆብ አምላክ የሰጠው ሥርዓት ነው። 5 እርሱ ይህን ትእዛዝ ለዮሴፍ ልጆች የሰጣቸው ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ነው። ያልታወቀ ድምፅ እንዲህ ሲል እሰማለሁ፤ 6 “እኔ ከትከሻችሁ ሸክምን አወረድኩላችሁ፤ የጡቡን ሸክም ከላያችሁ እንድትጥሉት አደረግሁ፤ 7 በመከራ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ ጠራችሁኝ፤ እኔም አዳንኳችሁ፤ ከመሰወሪያ ስፍራዬ፥ ከሞገድ ውስጥ ሰማኋችሁ፤ በክርክር ምንጮች አጠገብ ፈተንኳችሁ። 8 ሕዝቤ ሆይ! የማስጠንቀቂያ ንግግሬን ስማ! እስራኤል ሆይ! ብታዳምጡኝ ምንኛ መልካም ነበር! 9 ባዕድ አምላክ አይኑርህ፤ እርሱንም አታምልክ። 10 ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፤ ጠይቅ እንጂ የሚያስፈልግህን ሁሉ እሰጥሃለሁ። 11 “ሕዝቤ ግን እኔን አልሰማኝም፤ እስራኤል አልታዘዘልኝም። 12 ስለዚህ በልበ ደንዳናነታቸው አካሄድ እንዲሄዱ፥ የፈለጉትንም ነገር እንዲያደርጉ ተውኳቸው። 13 ሕዝቤ እኔን ቢሰማኝ፥ እስራኤልም እኔን ቢታዘዘኝ ኖሮ፥ 14 እኔ እግዚአብሔር ጠላቶቹን በኀያል ሥልጣኔ ድል በነሣሁለት ነበር። 15 እኔን የሚጠሉ ሁሉ በፍርሃት በእግሬ ሥር ይደፋሉ፤ ቅጣታቸውም ለዘለዓለም ይጸናል። 16 እናንተን ግን ጥሩ ስንዴ እመግባችኋለሁ፤ ከአለት ከሚገኘው ማርም አጠግባችኋለሁ።” |