2 ጴጥሮስ 3:10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያን ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል። ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረትም በታላቅ ግለት ይጠፋል፤ ምድርና በርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ወና ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ምድርም በእርሷም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፤ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። |
ፀሐይ፥ ጨረቃና ከዋክብት ሁሉ ይጠፋሉ፤ ሰማይም እንደ ብራና ተጠቅሎ ይወገዳል፤ ከዋክብትም እንደ ወይንና እንደ በለስ ዛፍ ቅጠል ይረግፋሉ።
ቀና ብላችሁ ወደ ሰማያት ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በነው ይጠፋሉ፤ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፤ በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ እንደ ዝንብ ይሞታሉ፤ የእኔ ማዳን ግን ዘለዓለማዊ ነው፤ ለታዳጊነቴም ፍጻሜ የለውም።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእህል ሰብል አጫጆች አጭደው ሳይጨርሱ፥ አራሾች የሚደርሱባቸውና ወይን ጨማቂዎችም የወይን ፍሬ ጨምቀው ሳይጨርሱ፥ የወይን ተካዮች የሚደርሱባቸው ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ተራራዎች ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያፈልቃሉ፤ ኰረብቶችም በወይን ጠጅ ይጥለቀለቃሉ።
መላዋ ምድር እንደ ግብጹ የዐባይ ወንዝ ከፍና ዝቅ በማለት ትናወጣለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሲነካ ትቀልጣለች፤ በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ።
በዚያን ጊዜ ሰም በእሳት እንደሚቀልጥና፥ ውሃም ከከፍተኛ ቦታ ወደ ታች እንደሚወርድ እንዲሁም ተራራዎች ከእርሱ ሥር ይቀልጣሉ፤ ሸለቆዎችም ይከፈታሉ።
በእግዚአብሔር ፊት ተራራዎች ይንቀጠቀጣሉ፤ ኰረብቶችም ይቀልጣሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት ምድር ትናወጣለች፤ ዓለምና በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ።
በኃጢአት የተሞላው የዚህ ሰው ሥጋ ይፈርስ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፋችሁ ልትሰጡት ይገባል። ይህንንም የምታደርጉት ጌታ ኢየሱስ ለፍርድ በሚመጣበት ቀን የዚህ ሰው ነፍስ እንድትድን ነው።
አሁን ስለ እኛ የምታውቁት በከፊል ነው፤ በኋላ ግን በሙላት እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚህም ምክንያት ጌታ ኢየሱስ በሚመጣበት ቀን እኛ በእናንተ እንደምንመካ እናንተም በእኛ ትመካላችሁ።
እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት በናፍቆት የምትጠባበቁና በቶሎም እንዲመጣ የምትሠሩ ሁኑ፤ በዚያን ቀን ሰማይ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል፤ ፍጥረቶችም በእሳት ግለት ይቀልጣሉ፤
እንዲሁም ማዕርጋቸውን ባለመጠበቅ ስፍራቸውን የተዉትን መላእክት አስታውሱ፤ እነርሱን እግዚአብሔር እስከ ታላቁ የፍርድ ቀን ድረስ በዘለዓለም እስራት፥ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጠብቆ አቆይቷቸዋል።
“እነሆ! እኔ እንደ ሌባ በድንገት እመጣለሁ! ራቁቱን እንዳይሆንና ኀፍረቱን ሰዎች እንዳያዩበት ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው የተመሰገነ ነው!”
ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያይቱ ምድር አልፈው ነበር፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።
እንግዲህ ምን ዐይነት ትምህርት እንደ ተቀበልክና እንደ ሰማህ አስታውስ፤ ጠብቀውም፤ ንስሓም ግባ፤ ባትነቃ ግን እንደ ሌባ በድንገት እመጣብሃለሁ፤ በምን ሰዓት ወደ አንተ እንደምመጣ አታውቅም።