1 ቆሮንቶስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ለመሆን ከተጠራው ከጳውሎስና ከወንድማችንም ከሶስቴንስ፦ 2 በቆሮንቶስ ከተማ ለምትገኘው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በውስጥዋም በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱትና ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩት፥ እንደዚሁም በየቦታው ለእነርሱና ለእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ለሚጠሩት ሁሉ። 3 ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ምስጋና ለእግዚአብሔር 4 በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋውን ስለ ሰጣችሁ በእናንተ ምክንያት ሁልጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። 5 በሁሉ ነገር በንግግርም ሆነ በዕውቀት በክርስቶስ በልጽጋችኋል። 6 ስለ ክርስቶስ የነገርናችሁ ምስክርነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል። 7 ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በመጠባበቅ ስትኖሩ ምንም ዐይነት መንፈሳዊ ስጦታ አይጐድልባችሁም፤ 8 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ያለነቀፋ ሆናችሁ ትገኙ ዘንድ እርሱ እስከ መጨረሻ ጸንታችሁ እንድትኖሩ ያደርጋችኋል። 9 ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። በክርስቲያኖች መካከል መለያየት ሊኖር እንደማይገባ 10 ወንድሞቼ ሆይ! “መለያየት በመካከላችሁ አይኑር፤ ሁላችሁም ተስማምታችሁ በአንድ ሐሳብና በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ ኑሩ” ብዬ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 11 ወንድሞቼ ሆይ! በመካከላችሁ ጠብ መኖሩን ከቀሎኤ ቤተሰብ ሰምቼአለሁ። 12 ይኸውም እናንተ እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔ የአጵሎስ ነኝ፤ እኔ የጴጥሮስ ነኝ፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ” ትላላችሁ። 13 ታዲያ ክርስቶስ ተከፋፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ የተጠመቃችሁት በጳውሎስ ስም ነውን? 14 እኔ ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ ማንንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 15 ስለዚህ “በእኔ በጳውሎስ ስም ተጠምቃችኋል” ብሎ መናገር የሚችል የለም። 16 (እርግጥ ነው፤ የእስጢፋኖስንም ቤተሰብ አጥምቄአለሁ፤ ከነዚህ ሌላ እኔ ያጠመቅሁት ሰው መኖሩን አላስታውስም፤) 17 ክርስቶስ የላከኝ የወንጌልን ቃል እንዳስተምር ነው እንጂ እንዳጠምቅ አይደለም፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር የወንጌልን ቃል የማስተምረው ከሰው ጥበብ በተገኘ ንግግር አይደለም። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጥበብና ኀይል መሆኑ 18 የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሰዎች እንደ ሞኝነት ይቈጠራል፤ ለምንድን ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው። 19 “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የሊቃውንትንም ዕውቀት አስወግዳለሁ” ተብሎ ተጽፎአል። 20 ታዲያ፥ ጥበበኛ የት አለ? የሕግ ምሁርስ የት አለ? ተመራማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት አድርጎት የለምን? 21 የዚህ ዓለም ሰዎች በገዛ ጥበባቸው እግዚአብሔርን ማወቅ እንዳይችሉ እግዚአብሔር በጥበቡ ዘጋባቸው፤ ነገር ግን እንደ ሞኝነት በሚቈጠረው እኛ በምናስተምረው ወንጌል የሚያምኑትን ለማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖአል። 22 መቼም አይሁድ ተአምር ማየትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎች ደግሞ ጥበብን ይሻሉ። 23 እኛ ግን ክርስቶስ ስለ እኛ መሰቀሉን እናስተምራለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናከያ ነው፤ ለግሪክ ሰዎች ደግሞ ሞኝነት ነው። 24 ለተጠሩት ግን ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ሰዎች፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። 25 የእግዚአብሔር ሞኝነት ነው ተብሎ የሚታሰበው ነገር ከሰው ጥበብ ይበልጣል፤ የእግዚአብሔር ደካማነት ነው ተብሎ የሚታሰበውም ነገር ከሰው ኀይል ይበልጣል። 26 ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔር በጠራችሁ ጊዜ ምን ዐይነት ሰዎች እንደ ነበራችሁ አስታውሱ፤ እንደ ሰው አስተሳሰብ ከእናንተ መካከል ብዙዎች ጥበበኞች ወይም ብርቱዎች ወይም ታላላቅ ሰዎች አልነበሩም። 27 እግዚአብሔር ጥበበኞችን ለማሳፈር በዓለም እንደ ሞኞች የሚቈጠሩትን ሰዎች መረጠ፤ ብርቱዎችንም ለማሳፈር በዓለም እንደ ደካሞች የሚቈጠሩትን መረጠ፤ 28 እግዚአብሔር በዓለም ሰዎች ዘንድ አሉ ተብለው የሚታዩትን ነገሮች እንደሌሉ ለማድረግ በዓለም የተዋረደና የተናቀ ከንቱም መስሎ የሚታየውን ነገር መረጠ። 29 ይህንንም ያደረገው ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ ነው። 30 እናንተን ግን እግዚአብሔር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አደረገ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ጥበባችን፥ ጽድቃችን፥ ቅድስናችንና ቤዛችን እንዲሆን አደረገው። 31 እንግዲህ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈው “የሚመካ በጌታ ይመካ።” |