Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ጴጥሮስ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጌታ ኢየሱስ የመምጣት ተስፋ

1 ወዳጆች ሆይ! ይህ የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው፤ በሁለቱም መልእክት ቅን ልቡናችሁን በማሳሰብ አነቃቃለሁ።

2 ከዚህ በፊት በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል፥ እንዲሁም በሐዋርያዎቻችሁም አማካይነት ያገኛችኋትን የጌታችንንና የመድኃኒታችንን ትእዛዝ እንድታስቡ ይገባል።

3 ከሁሉ በፊት ይህን አስተውሉ፤ በመጨረሻው ዘመን እንደራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ እወቁ፤

4 እነርሱም “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ፥ የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ፥ ሁሉ እንዳለ ይኖራል” ይላሉ።

5 እነዚህ ሰዎች ከብዙ ዘመን በፊት ሰማያት በእግዚአብሔር ቃል መፈጠራቸውን ምድርም የተሠራችው ከውሃና በውሃ መሆኑን ሆን ብለው አያስተውሉም።

6 በዚህም ምክንያት ያንጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ፤

7 ነገር ግን አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር በዚሁ ቃል፥ እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀው ይቆያሉ።

8 ወዳጆች ሆይ! እናንተ ግን በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።

9 አንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው፥ ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃና ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።

10 የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ምድርም በእርሷም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።

11 እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል መኖር አይገባችሁም?

12 እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት የምትጠባበቁ የምታፋጥኑ ሁኑ፤ ምክንያቱም ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የፍጥረት መሰረተ ነገር በእሳት ግለት ይቀልጣሉ!

13 ነገር ግን እኛ ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።

14 ስለዚህ ወዳጆች ሆይ! ይህን ሁሉ እየተጠባበቃችሁ፥ ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ኑሩ፤

15 የጌታችንም ትዕግሥት ለእናንተ መዳን እንደሆነ ቁጠሩ። እንደዚሁ የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤

16 በመልእክቶቹም ሁሉ እንዳደረገው ስለዚህ ነገር ተናግሯል። በመልእክቶቹ ውስጥ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ፤ ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ ሁሉ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።

17 እንግዲህ ወዳጆች ሆይ! እናንተስ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፥ በዐመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከጽኑ አቋማችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤

18 ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም ለዘለዓለምም ክብር ይሁን! አሜን።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos