Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


1 ቆሮንቶስ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በምእመናን መካከል የተደረገ ምግባረ ብልሹነት

1 በመካከላችሁ አሳፋሪ የዝሙት ሥራ መኖሩ ይወራል፤ እንዲህ ዐይነቱ የዝሙት ሥራ በአሕዛብ ዘንድ እንኳ የማይደረግ ነው፤ ይኸውም የእንጀራ እናቱን እንደ ሚስት አድርጎ የሚኖር አለ ተብሎአል።

2 ታዲያ፥ እንዲህ ያለ አሳፋሪ ነገር በመካከላችሁ እያለ ለምን ትታበያላችሁ? ይልቅስ በዚህ ነገር ማዘን አይገባችሁምን? እንዲህ ዐይነቱን ሥራ የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱ።

3 ምንም እንኳ እኔ በሥጋ አብሬአችሁ ባልሆን በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ልክ አብሬአችሁ እንዳለሁ ሆኜ እንዲህ ዐይነቱን ሥራ በፈጸመው ሰው ላይ በጌታ በኢየሱስ ስም ፈርጄበታለሁ፤

4 በምትሰበሰቡበት ጊዜ እኔም በጌታችን በኢየሱስ ኀይል በመካከላችሁ በመንፈስ ስለምገኝ፥

5 በኃጢአት የተሞላው የዚህ ሰው ሥጋ ይፈርስ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፋችሁ ልትሰጡት ይገባል። ይህንንም የምታደርጉት ጌታ ኢየሱስ ለፍርድ በሚመጣበት ቀን የዚህ ሰው ነፍስ እንድትድን ነው።

6 እንግዲህ መመካታችሁ መልካም አይደለም፤ ትንሽ እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው ታውቁ የለምን?

7 አሁን እንደ ሆናችሁት ሁሉ እርሾ እንደሌለበት እንደ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ የፋሲካችን በግ የሆነው ክርስቶስ ተሠውቶአል፤

8 ስለዚህ ተንኰልና ክፋት በሞላበት በአሮጌ እርሾ ሳይሆን እርሾ በሌለበት የቅንነትና የእውነት ቂጣ በዓላችንን እናክብር።

9 ከዚህ በፊት በጻፍኩላችሁ መልእክት ከአመንዝራዎች ጋር አትተባበሩ ብያችሁ ነበር።

10 ይህንንም ስል በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም አመንዝራዎች ወይም ከስግብግብ ግለሰቦች ወይም ከሌቦች ወይም ከጣዖት አምላኪዎች ጋር አትተባበሩ ማለቴ አይደለም፤ እንዲህማ ከሆነ ከዓለም መውጣት ያስፈልጋችሁ ነበር ማለት ነው።

11 እኔ ግን የጻፍኩላችሁ ክርስቲያኖች ተብለው ከሚያመነዝሩ፥ ወይም ከሚስገበገቡ፥ ወይም ጣዖት ከሚያመልኩ፥ ወይም የሰውን ስም ከሚያጠፉ፥ ወይም ከሚሰክሩ፥ ወይም ከቀማኞች ጋር አትተባበሩ ብዬ ነው። እንደእነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር፥ መብል አብራችሁ አትብሉ።

12 ከክርስቲያናዊ ማኅበር ውጪ ባሉት ሰዎች ላይ ለመፍረድ እኔ ማን ነኝ? በክርስቲያናዊ ማኅበር ውስጥ ስላሉት ሰዎች ጉዳይ እናንተስ መፍረድ ትችሉ የለምን?

13 በውጪ ስላሉት ሰዎች ጉዳይ የሚፈርድ እግዚአብሔር ነው፤ እንግዲህ መጽሐፍ እንደሚል “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos