ኤርምያስ 7:13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንተ ይህን ሁሉ በደል ፈጸማችሁ፤ ደጋግሜ ብነግራችሁም አናዳምጥም ብላችኋል፤ በጠራኋችሁም ጊዜ መልስ አልሰጣችሁኝም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሁንም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ ይላል ጌታ፥ በማለዳም ተነሥቼ ባለማቋረጥ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አሁንም ይህን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ ተናገርኋችሁ፤ ነገር ግን አልሰማችሁም፤ ጠራኋችሁም፤ ነገር ግን አልመለሳችሁም፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሁንም ይህን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ በማለዳም ተነሥቼ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥ |
“እኔ በመጣሁ ጊዜ ማንም ሰው አለመኖሩ ለምንድን ነው? በጠራሁም ጊዜ ማንም ሰው መልስ ያልሰጠኝ ለምንድን ነው? እኔ ለመታደግ አልችልምን? ለማዳንስ ኀይል የለኝምን? በተግሣጼ ብቻ ባሕርን አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ወደ ምድረ በዳነት እለውጣለሁ፤ ዓሣዎቻቸውም ውሃ ከማጣት የተነሣ ሞተው ይበሰብሳሉ።
ስለዚህ እናንተ በጠራኋችሁ ጊዜ መልስ ስላልሰጣችሁና በተናገርኩም ጊዜ ስላላዳመጣችሁ ለእኔ መታዘዝን ትታችሁ ክፉ ማድረግን ስለ መረጣችሁ ዕድል ፈንታችሁ ለገዳይ ተንበርክኮ በሰይፍ መገደል ይሆናል።”
ስጠራ ማንም ስላልመለሰልኝ፥ ስናገር ማንም ስላላዳመጠኝ ነገር በፊቴ ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጉና የማያስደስተኝን ስለ መረጡ እኔም በእነርሱ ላይ ቅጣት አመጣባቸዋለሁ።”
የቀድሞ አባቶቻቸውን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ለእኔ እንዲታዘዙ ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው፤ ሕዝቡንም እስከ ዛሬው ቀን ድረስ እንኳ ከማስጠንቀቅ አልተቈጠብኩም።
ነገር ግን ሊያዳምጡኝም ሆነ ሊታዘዙኝ አልፈለጉም፤ በዚህ ፈንታ እያንዳንዱ ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኛና ክፉ ሆኖአል፤ ቃል ኪዳኔን እንዲፈጽሙ አዘዝኳቸው፤ እነርሱ ግን እምቢ አሉ፤ ስለዚህ በቃል ኪዳኔ የተጻፈውን መቅሠፍት ሁሉ አመጣሁባቸው።”
እነዚህ በክፋት የተሞሉ ሕዝብ ለእኔ መታዘዝን እምቢ ብለዋል፤ ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኞች ሆነዋል፤ ባዕዳን አማልክትን በማምለክ ያገለግላሉ፤ ከዚህም የተነሣ እነርሱ ዋጋቢስ ሆኖ እንደ ቀረው እንደዚያ መታጠቂያ ይሆናሉ።
መታጠቂያ በወገብ ዙሪያ ተጣብቆ እንደሚገኝ፥ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ከእኔ ጋር እንዲጣበቁ ዐቅጄ ነበር፤ ይህንንም ያደረግኹት ሕዝቤ እንዲሆኑና ለስሜ ምስጋናና ክብር እንዲያስገኙ ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙኝም።”
“የዓሞን ልጅ ኢዮስያስ በይሁዳ ከነገሠ ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ ለኻያ ሦስት ዓመት ሲናገረኝ ቈይቶአል፤ የእርሱንም ቃል ለእናንተ ከመናገር ከቶ አልቦዘንኩም፤ እናንተ ግን ልብ ብላችሁ አላስተዋላችሁም፤
የኢዮናዳብ ዘሮች እንኳ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ አባታቸው ያዘዛቸውን ቃል በመጠበቅ እነሆ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዐይነት የወይን ጠጅ አይቀምሱም፤ እኔ ግን ሁልጊዜ በመደጋገም እነግራችኋለሁ፤ እናንተ ልትታዘዙኝ አልፈለጋችሁም፤
አገልጋዮቼ የሆኑትን ነቢያትን ወደ እናንተ ደጋግሜ ልኬአለሁ፤ እነርሱም ከክፉ ሥራችሁ ተመልሳችሁ ቅን የሆነውን ነገር እንድትሠሩ ነግረዋችኋል፤ ለባዕዳን አማልክት እንዳትሰግዱና የእነርሱም አገልጋዮች እንዳትሆኑ አስጠንቅቀዋችኋል፤ ለእናንተና ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋችሁ ምድር መኖር ትችሉ ዘንድ ይህን ሁሉ አዘዝኳችሁ፤ እናንተ ግን እኔን ለማዳመጥም ሆነ ለምነግራችሁ ቃል ትኲረት ልትሰጡት አልፈለጋችሁም።
ስለዚህም እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አደርስባችኋለሁ ብዬ የተናገርኩትን ጥፋት ሁሉ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሆናችሁት ሁሉ ላይ አመጣባችኋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ስነግራችሁ ባለማዳመጣችሁና ስጠራችሁም መልስ ባለመስጠታችሁ ነው።”
ይህም ሁሉ መቅሠፍት የደረሰባችሁ ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት በማቅረባችሁ፥ እግዚአብሔርን በማሳዘናችሁ፥ ለሕጉ፥ ለድንጋጌውና ለሥርዓቱም ባለመታዘዛችሁ ነው።”
እኔም መልሼ እንዲህ አልኩ፦ “እኔ ብነግራቸውና ባስጠነቅቃቸው ማን ሊሰማኝ ይችላል? እነርሱ እልኸኞች ስለ ሆኑ፥ ቃልህን መስማት አይፈልጉም፤ የአንተን ቃል ስነግራቸው በንቀት መሳቂያ ያደርጉኛል።
የቀድሞ አባቶቻችሁ ከግብጽ ከወጡበት ቀን አንሥቶ እስከዚህች ቀን ድረስ አገልጋዮቼን ነቢያትን እያከታተልኩ ከመላክ የተቈጠብኩበት ጊዜ የለም።
ነገር ግን ሕዝቤን እስራኤልን ይበልጥ ወደ እኔ እንዲቀርቡ በጠራኋቸው መጠን፥ እነርሱ ይበልጥ ከእኔ እየራቁ ሄዱ። በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት ከማቅረብና ለምስሎቹም ዕጣን ከማጠን አልተቈጠቡም።
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ! ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ፥ እኔም የአንቺን ልጆች በአንድነት ልሰበስብ ስንት ጊዜ ፈቀድኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።