Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢየሩሳሌም በጠላት መከበብ

1 የብንያም ሕዝብ ሆይ! ሕይወታችሁን ለማትረፍ ሽሹ! ከኢየሩሳሌምም ውጡ! በተቆዓ የጥሩምባ ድምፅ አሰሙ፤ በቤትሀካሬም ለምልክት የሚሆን እሳት አንድዱ! መቅሠፍትና ጥፋት ከሰሜን በኩል ሊመጣ ነው።

2 ውብና አስደሳች የሆነችው የጽዮን ከተማ ትጠፋለች።

3 እረኞች ከነመንጋቸው እዚያ ይሰፍራሉ፤ ድንኳኖቻቸውን በከተማይቱ ዙሪያ ይተክላሉ፤ እያንዳንዱም ደስ ባለው ስፍራ መንጋውን ያሰማራል።

4 ጠላቶችዋም እንዲህ ይላሉ፦ “ኢየሩሳሌምን ለመውጋት እንዘጋጅ! ተነሡ! በእኩለ ቀን ላይ አደጋ እንጣልባት! እንዲያውም ዘግይተናል፤ ቀኑ ሊመሽ ተቃርቦአል፤ ፀሐይም ልትጠልቅ በመቃረብዋ ጥላው እየረዘመ ሄዶአል፤

5 ስለዚህ ተነሡ፥ በሌሊት አደጋ ጥለን የከተማይቱን ምሽጎች እናፈራርስ።”

6 ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዛፎችን ቊረጡ፤ በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደምሽግ ሆኖ የሚያገለግል ዐፈር ቈልሉ፤ እርስዋ በግፍ የተሞላች ስለ ሆነ መቀጣት የሚገባት ከተማ ናት፤

7 ጒድጓድ ውሃን እንደሚያፈልቅ፥ ኢየሩሳሌምም የክፋት ሁሉ መፍለቂያ ናት፤ በእርስዋ የሚሰማው የግፍና የጥፋት ጩኸት ብቻ ነው፤ ዘወትር የሚታይባትም ሕመምና ቊስል ነው።

8 እናንተ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ይህ ሁሉ መከራ ማስጠንቀቂያ ይሁናችሁ፤ አለበለዚያ ከፊቴ አስወግዳችኋለሁ፤ ከተማችሁን ወደ ምድረ በዳ ለውጬ ማንም እንዳይኖርባት አደርጋለሁ።”


የእስራኤል ዐመፀኛነት

9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከእስራኤል የተረፉትን የወይን ዘለላን እንደሚለቅም ሰው ልቀሙ፤ መላልሳችሁ ወይንን እንደሚለቅም ሰው እጃችሁን በቅርንጫፎቹ ላይ ዘርጉ።”

10 እኔም መልሼ እንዲህ አልኩ፦ “እኔ ብነግራቸውና ባስጠነቅቃቸው ማን ሊሰማኝ ይችላል? እነርሱ እልኸኞች ስለ ሆኑ፥ ቃልህን መስማት አይፈልጉም፤ የአንተን ቃል ስነግራቸው በንቀት መሳቂያ ያደርጉኛል።

11 ጌታ ሆይ! አንተ በእነርሱ ላይ ያለህ ቊጣ በእኔም ውስጥ ይነዳል። ከቶም ልታገሠው አልችልም።” እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “ቊጣዬን በመንገድ ላይ በሚገኙ ሕፃናትና በተሰበሰቡ ወጣቶች ላይ አፍስሰው፤ ባልና ሚስት በአንድነት ይወሰዳሉ፤ በዕድሜ ለገፉ ሽማግሌዎች እንኳ ምሕረት አይደረግላቸውም።”

12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የዚህችን ምድር ሕዝብ በምቀጣበት ጊዜ ቤቶቻቸው፥ እርሻዎቻቸውና ሚስቶቻቸው ጭምር ለሌሎች ይሰጣሉ።

13 ታላላቆችም ሆኑ ታናናሾች እያንዳንዱ ሰው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ጥቅሙን ያግበሰብሳል፤ ነቢያትና ካህናት ሳይቀሩ ሕዝቡን ያታልላሉ፤

14 የሕዝቤንም የስብራት ቊስል እንደ ቡጭራት በመቊጠር በሚገባ አያክሙትም፤ እንዲሁም ሰላም ሳይኖር ‘ሰላም ነው፤ ሰላም ነው፤’ ይላሉ።

15 ይህን ሁሉ አጸያፊ ነገር ሠርተው ኀፍረት ተሰምቶአቸው ነበርን? እንኳንስ ሊያፍሩ ቀርቶ ዐይናቸው እንኳ ሰበር አላለም፤ ስለዚህ ሌሎች እንደ ወደቁ እነርሱም ይወድቃሉ፤ እኔ በምቀጣቸው ጊዜ ፍጻሜአቸው ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”


የእስራኤል ከእግዚአብሔር መንገድ መውጣት

16 እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “በየጐዳናው ቆማችሁ ተመልከቱ፤ ጥንታዊና መልካም የሆነችው መንገድ የትኛዋ እንደ ሆነች ጠይቃችሁ ተረዱ፤ ባገኛችኋትም ጊዜ በእርስዋ ሂዱ፤ በሰላምም ትኖራላችሁ።” ሕዝቡ ግን “በእርስዋ አንሄድም!” አሉ።

17 ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር የማስጠንቀቂያውን ጥሩምባ ድምፅ የሚያሰሙ ጠባቂዎችን አቆመ፤ እነርሱ ግን “አንሰማም” አሉ።

18 ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሕዝቦች ስሙ! በሕዝቤ ላይ የማደርገውንም ሁሉ አስተውሉ።

19 ምድር ሆይ! ስሚ! እነርሱ ያስተማርኳቸውን ሥርዓት ስለ ተቃወሙ፤ ለሕጌም ስላልታዘዙ ስለ ክፉ ሐሳባቸው ሁሉ እቀጣቸው ዘንድ በሕዝቡ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ።

20 ከሳባ የሚያመጡልኝ ዕጣን፥ ከሩቅ አገሮች የሚያመጡልኝ ቅመማቅመም ሁሉ ለእኔ ምን ይረባኛል? መባቸውን አልቀበለውም፤ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘኝም።

21 ስለዚህ ይህ ሕዝብ ተሰናክሎ እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች፥ ጓደኛሞችና ጐረቤቶች በአንድነት ይሞታሉ።”


ከሰሜን በኩል የሚቃጣ ወረራ

22 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሰሜን በኩል ከሚገኝ አገር ወራሪ ይመጣል፤ በሩቅ ያለ ታላቅ ሕዝብም ለጦርነት ተዘጋጅቶአል፤

23 ቀስታቸውንና ሰይፋቸውን አንሥተዋል፤ እነርሱም ምሕረት የሌላቸው ጨካኞች ናቸው፤ ተቀምጠው የሚጋልቡአቸው ፈረሶች፥ የኮቴአቸው ድምፅ እንደ ባሕር ሞገድ ነው። እነሆ እነርሱ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት ተዘጋጅተዋል።”

24 የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “ወሬውን ስለ ሰማን ክንዳችን ዛለ፤ በምጥ እንደ ተያዘች ሴትም ጭንቀትና ሕመም ተሰምቶናል፤

25 ወደ እርሻ አትውጡ፤ በመንገድ ላይም አትዘዋወሩ፤ በየአቅጣጫው ሽብር ስለ ሆነ ከጠላት ሰይፍ ተጠንቀቁ።”

26 እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “ሊያጠፋችሁ የመጣው ጠላት በድንገት አደጋ ሊጥልባችሁ ስለ ሆነ፥ ማቅ ለብሳችሁ በዐመድ ላይ ተንከባለሉ፤ አንድ ልጁ እንደ ሞተበት ሰው ምርር ብላችሁ አልቅሱ፤

27 ኤርምያስ ሆይ! ብረት እንደሚፈተን ሕዝቤን ፈትነህ ምን ዐይነት እንደ ሆኑ ዕወቅ፤

28 ሁሉም እንደ ነሐስና እንደ ብረት የጠነከሩ፤ በእልህም የተወጠሩ ዐመፀኞች ናቸው። ሁሉም የተበላሹ የሐሜት ሱሰኞች ናቸው፤

29 እርሳሱን በእሳት ለማቅለጥ ወናፉ በኀይል ያናፋል፤ ክፉዎች ስላልተወገዱ ግን አንጥረኛው በከንቱ ይደክማል።

30 እኔ እግዚአብሔር ስለ ጣልኳቸው ‘ንጹሕ ባለመሆኑ የወደቀ ብር’ ብለው ይጠሩአቸዋል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos