Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኤርምያስ በባቢሎን ለሚኖሩ አይሁድ የላከው ደብዳቤ

1 ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ለወሰዳቸው ካህናትና ነቢያት ለሕዝብ አለቆችና ለሌሎችም ስደተኞች ሁሉ ከኢየሩሳሌም የጻፍኩት ደብዳቤ ይዘት እንዲህ የሚል ነው፤

2 ደብዳቤውንም የጻፍኩት ንጉሡ ኢኮንያን፥ እቴጌይቱ እናቱና የቅርብ አገልጋዮቹ፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌም መሪዎች፥ የእጅ ጥበብ ሠራተኞችና ሙያተኞች ሁሉ ተማርከው ከተወሰዱ በኋላ ነው፤

3 ደብዳቤውንም የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላካቸው በሻፋን ልጅ በኤልዓሳና በሕልቂያ ልጅ በገማርያ እጅ ላክሁት፤ የደብዳቤውም ፍሬ ነገር እንዲህ የሚል ነው፦

4 “ከኢየሩሳሌም አስማርኮ ወደ ባቢሎን ላስወሰዳቸው ሕዝብ ሁሉ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦

5 ‘ቤት ሠርታችሁ ኑሩ፤ አትክልት ትከሉ፤ ፍሬውንም ብሉ፤

6 እየተጋባችሁ ልጆችን ውለዱ፤ ልጆቻችሁም በተራቸው እየተጋቡ ልጆችን ይውለዱ፤ ቊጥራችሁ ይብዛ እንጂ አይቀንስ፤

7 ተማርካችሁ ሄዳችሁ እንድትኖሩባቸው ላደረግኋቸው ከተሞችም ዕድገት መልካም ነገርን ተመኙ፤ ስለ እነርሱም መልካም ኑሮ ወደ እኔ ጸልዩ፤ እነርሱ መልካም ኑሮ ቢኖሩ እናንተም መልካም ኑሮን ትኖራላችሁ።

8 እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ በመካከላችሁ በሚኖሩ ነቢያት ወይም የወደፊቱን ሁኔታ እናውቃለን በሚሉ ሰዎች ሁሉ እንዳትታለሉ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ለሕልሞቻቸውም ትኲረት አትስጡአቸው።

9 እነርሱ በእኔ ስም የሚነግሩአችሁ ትንቢት ሁሉ ሐሰት ነው፤ እኔ ከቶ አላክኋቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”

10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በባቢሎን የምትኖሩበት ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ እንደገና እናንተን በምሕረት እጐበኛለሁ፤ ወደ አገራችሁ እንድመልሳችሁ የገባሁትን ቃል ኪዳን እፈጽማለሁ፤

11 ስለ እናንተ ያለኝን ዕቅድ የማውቅ እኔ ነኝ፤ ይህም ዕቅድ ክፋትን ሳይሆን ሰላምን በማስገኘት እናንተ በተስፋ የምትጠብቁት መልካም ነገር የሚፈጸምበት ነው፤

12 ከዚያን በኋላ እናንተ ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ፤

13 ትፈልጉኛላችሁ፤ የምትፈልጉኝም በሙሉ ልባችሁ ከሆነ ታገኙኛላችሁ፤

14 በእርግጥ እላችኋለሁ ታገኙኛላችሁ፤ እኔም ወደ ምድራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ እናንተን ከበተንኩበት ከየትኛውም አገርና ከየትኛውም ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ እኔ እናንተን ነቅዬ እንድትሰደዱ ከማድረጌ በፊት ወደ ነበራችሁበት ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

15 “እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል” ብላችሁ ተናግራችኋል።

16 የዳዊትን ዙፋን ወርሶ ገዢ ስለ ሆነው ንጉሥና እንደ እናንተ ተማርከው ስላልተወሰዱት በዚህች ከተማ ስለሚገኙት ዘመዶቻችሁ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ስሙ።

17 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ በእነርሱ ላይ ጦርነትን፥ ራብንና ቸነፈርን ላመጣባቸው ነው፤ ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበሉት እንደማይቻል የበለስ ዛፍ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ፤

18 በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር አባርራቸዋለሁ፤ የዓለም ሕዝብ ሁሉ በእነርሱ ላይ ስለሚያዩት ነገር ይደነግጣሉ፤ እንዲበተኑ በማደርግበት ስፍራ ሁሉ በእነርሱ ላይ የማደርሰውን ነገር የሚያዩ ሕዝቦች ሁሉ በመደንገጥ ይሸበራሉ። ሕዝብም ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ ያደርጋቸዋል።

19 ይህም ሁሉ የሚደርስባቸው በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት በመደጋገም የላክሁላቸውን ቃሌን ካለመስማትና ካለመታዘዝ የተነሣ ነው።

20 ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን እንድትሰደዱ ያደረግኋችሁ እናንተም ሁላችሁ እኔ እግዚአብሔር የምለውን ቃል ስሙ።”

21 “በእግዚአብሔር ስም የሐሰት ትንቢት ቃል ስለሚነግሩአችሁም ስለ ቆላያ ልጅ አክዓብና ስለ ማዕሤያ ልጅ ሴዴቅያስ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፦ ‘እነርሱን ዐይናችሁ እያየ በፊታችሁ በሞት ለሚቀጣቸው ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤

22 ከኢየሩሳሌም ተማርከው ወደ ባቢሎን የተሰደዱ ሕዝብ ሁሉ በአንድ ሰው ላይ የእርግማን ቃል መናገር ሲፈልጉ፥ ‘እግዚአብሔር የባቢሎን ንጉሥ በሕይወት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግህ’ ይላሉ፤

23 ዕድል ፈንታቸውም ይህ የሚሆንበት ምክንያት አሠቃቂ ኃጢአት በመሥራታቸው ነው፤ ይኸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ጋር አመንዝረዋል፤ እኔም ያላዘዝኳቸውን የሐሰት ቃል በስሜ ተናግረዋል፤ ይህም እኔ ያልፈቀድኩት ነገር ነው፤ ያደረጉትን ሁሉ ስለማውቅባቸው በእነርሱ ላይ እመሰክርባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”


ሸማዕያ የላከው ደብዳቤ

24-25 የኔሔላም ተወላጅ ለሆነው ለሸማዕያ፥ እንዲህ በለው፤ ይህ የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ ቃል ነው፤ ለኢየሩሳሌም ሰዎች ለካህኑ ለማዕሲያ ልጅ ለሰፎንያስና ለሌሎቹም ካህናት በራስህ ስም መልእክቶችን ልከሃል፤ በመልእክትህም ለሰፎንያስ እንዲህ ብለኸዋል፦

26 “እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ቦታ ካህን አድርጎ ሾሞሃል፤ እነሆ የቤተ መቅደሱም የበላይ አለቃ አንተ ነህ፤ ስለዚህም ነቢይ ነኝ እያለ በማስመሰል የሚናገረውን አንዳንድ ዕብድ በአንገት ሰንሰለትና በእግር ግንድ እየጠፈሩ ማሰር የአንተ ተግባር መሆን አለበት፤

27 ታዲያ ነቢይ ነኝ እያለ ለሕዝቡ የሚናገረውን የዐናቶት ተወላጅ የሆነውን ኤርምያስን ለምን አልገሠጽከውም?

28 እርሱ እንዳይናገር መከልከል አለበት፤ ምክንያቱም ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱት ሕዝብ ገና ብዙ ዘመን መኖር እንዳለባቸው በመቊጠር ‘ቤት ሠርታችሁ ተደላድላችሁ ኑሩ፤ አትክልት ትከሉ፤ ፍሬውንም ብሉ’ እያለ ለሕዝቡ ተናግሮአል።”

29 ሶፎንያስ ደብዳቤውን ለእኔ ለኤርምያስ አነበበልኝ፤

30 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

31 “እነሆ ተሰደው በባቢሎን ወደሚኖሩት ሁሉ ስለ ሽማዕያ የተነገረውን ይህን የትንቢት ቃል እንዲህ ብለህ ላክ፥ ‘ሽማዕያ እኔ ሳልከው የትንቢት ቃል በመናገር በውሸት እንድታምኑ አድርጓችኋል፤

32 ስለዚህም እኔ እግዚአብሔር እርሱንና ዘሮቹን ሁሉ እቀጣለሁ፤ ከእንግዲህ ይህ ሰው በእናንተ መካከል የሚተርፍ ዘር አይኖረውም፤ እርሱ ራሱም ለሕዝቤ የማደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ለማየት የመኖር ተስፋ የለውም፤ ምክንያቱም እርሱ እናንተን በእኔ ላይ እንድታምፁ አድርጓችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos