ሆሴዕ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሆሴዕ በእስራኤል ላይ ቅጣት እንደሚመጣ መናገሩ 1 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በየዐውድማው የሚገኘውን የዝሙት ዋጋ ከበዓል የሚሰጥ በረከት መስሎአችሁ፥ ትወዱታላችሁ፤ ይህን በማድረጋችሁ ለአምላካችሁ ታማኞች ሆናችሁ አልተገኛችሁም፤ ስለዚህ እንደ ሌሎች ሕዝቦች መደሰታችሁንና ሐሴት ማድረጋችሁን ተዉ! 2 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ከዐውድማችሁ እህልን፥ ከመጭመቂያችሁም የወይን ጠጅን ከቶ አታገኙም፤ አዲስ የወይን ጠጅም አይገኝም። 3 የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር በሰጣቸው ምድር አይኖሩም፤ ነገር ግን ተገደው ወደ ግብጽ ይመለሳሉ፤ ወደ አሦርም ሄደው በሥርዓት ንጹሕ ያልሆነ ምግብ ይበላሉ። 4 በዚያም ለእግዚአብሔር የወይን ጠጅ መባ ማቅረብ አይችሉም፤ መሥዋዕታቸውም እግዚአብሔርን አያስደስትም፤ የእነርሱ እንጀራ ሲርባቸው የሚበሉት እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ አይደለም፤ ስለዚህ ለእነርሱ የእዝን እንጀራ ይሆናል፤ እርሱንም የሚመገብ ሁሉ ይረክሳል። 5 እንግዲህ ለእግዚአብሔር ክብር በተወሰኑት የዓመት በዓላት ምን ታደርጋላችሁ? 6 እነሆ ከጥፋት ለማምለጥ ሲሸሹ ግብጽ ትሰበስባቸዋለች፤ ሜምፊስ ትቀብራቸዋለች፤ ያከማቹት የብር ሀብት ሁሉ ሳማ ለብሶ ይቀራል፤ መኖሪያቸውም እሾኽ ይበቅልበታል። 7 የቅጣት ቀን ደርሶአል፤ እስራኤላውያንም የበቀል ቀን መቃረቡን ይወቁ፤ በእናንተ በደልና ጥላቻ ምክንያት ነቢይን እንደ ሞኝ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበትን ሰው እንደ ዕብድ ትቈጥሩታላችሁ። 8 እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ነቢዩ ጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል፤ ሆኖም በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ ተዘርግቶበታል፤ በአምላኩም ቤተ መቅደስ ጥላቻ ይጠብቀዋል። 9 የእስራኤል ሕዝብ በገባዖን ዘመን እንደ ነበሩት ሰዎች በጣም ረክሰዋል፤ እግዚአብሔርም በደላቸውን አስቦ ስለ ኃጢአታቸው ይቀጣቸዋል። የእስራኤል ሕዝብ ኃጢአትና ያስከተለው ውድቀት 10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤልን ባገኘሁ ጊዜ የወይን ዘለላን ከምድረ በዳ እንደ ማግኘት ነበር፤ የቀድሞ አባቶቻችሁን ባየሁ ጊዜ ቀድሞ የጐመራውን የበለስ ፍሬ እንደማየት ነበር፤ ወደ በዓል ጴዖር በደረሱ ጊዜ ግን ራሳቸውን ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ለይተው አቀረቡ፤ እነርሱም እንደዚያ እንደሚወዱት ጣዖት የረከሱ ሆኑ። 11 የእስራኤል ሕዝብ ታላቅነት እንደ ወፍ በሮ ይጠፋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ መፅነስ የለም፤ ማርገዝ የለም፤ መውለድም የለም። 12 ልጆች ወልደው ቢያሳድጉም ሁሉንም ስለምቀሥፋቸው ልጅ አልባ ሆነው ይቀራሉ፤ እኔ ከእነርሱ በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!” 13 እስራኤልን በመልካም መሬት ላይ እንደ ተተከለች የዘንባባ ዛፍ ሆና አየኋት፤ እስራኤላውያን ግን ልጆቻቸውን ለዕርድ አቀረቡ። 14 ጌታ ሆይ! ለዚህ ሕዝብ ምን ትሰጠው፤ የሚጨነግፍ ማሕፀንና ደረቅ ጡት ስጣቸው! የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ላይ 15 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ገና በጌልገላ ሳሉ ክፉ ሥራቸው ተገለጠ፤ እኔም በዚያ የእነርሱን ሥራ መጥላት ጀመርኩ፤ ስለ ሠሩትም ክፉ ሥራ ከሰጠኋቸው ምድር አስወጣቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ለእነርሱ ፍቅር አላሳያቸውም፤ መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ሆነዋል። 16 የእስራኤል ሕዝብ ነፋስ እንደ መታው፥ ሥሩ እንደ ደረቀና ማፍራት እንደማይችል ዛፍ ያለ ፍሬ ይቀራሉ፤ ልጆች ቢወልዱም እጅግ የሚወዱአቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።” ነቢዩ ስለ እስራኤል የተናገረው የትንቢት ቃል 17 እርሱን ስላልታዘዙ አምላኬ ይጥላቸዋል፤ እነርሱም በአሕዛብ መካከል በመንከራተት ይኖራሉ። |