ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የእስራኤል ሕዝብ በጣኦት አያመልክም፥ 1 አንተ አምላካችን ግን ደግና እውነተኛ፥ በቶለ የማትቆጣ፥ ዓለምን በምሕረትህ የምትገዛ ነህ። 2 ብንበድል እንኳ እኛ ያንተ ነን፤ ሥልጣንህንም እንቀበላለን፤ ግን ያንተ መሆናችንንም ስለምናውቅ አንበድልም። 3 አንተን ማወቅ ፍጹም ቀናነት ነው፤ ጌትነትህን መቀበል ሕያው ሆኖ የመኖር መሠረት ነው። 4 ያለ ቦታቸው በዋሉ የሰው ልጅ ጥበብ ግኝቶች፥ ወይም በሠዓሊዎች ፍሬቢስ የፈጠራ ሥራዎች፥ 5 ሞኞችን በሚያማልሉ ግዑዝና ትንፋሽ አልባ ምስሎችም አልተታለልንም። 6 እነርሱን የሚሠሩ፥ እነርሱን የሚሹ፥ እነርሱንም የሚያመልኩ፥ የክፋት ወዳጆችና እንደነዚህ ላሉ ፍሬቢስ ተስፋዎች የተገቡ ናቸው። ጣኦት ቀራጮች አላዋቂዎች ናቸው 7 ሸክላ ሠሪው ለስላሳውን አፈር ለውሶ፥ ቀርጾና ደክሞ እኛ የምንገለገልባቸውን ቁሳቁሶች ይሠራል፤ ለከበረ ዓላማ የሚውለውን ዕቃ ለረከሰውም ቢሆን እንዲሁ የሚሠራው ከዚያው ጭቃ ነው። ከሁለቱ ግልጋሎቶች የትኛው ለየትኛው እንደሚውልም የሚወስነው እርሱ ነው። 8 ከንቱ ድካም እርሱ ራሱ በቅርቡ ከወጣበት አፈር፥ ብዙም ሳይቆይ የተዋሳትን ነፍስ እንዲመልስ በተጠየቀ ጊዜ ከሚገባበት ምድር፥ ከዚያው ጭቃ ፍሬ ቢሱን ጣኦት ቀረጸ። 9 ከዚህ ሁሉ በኋላም ስለ ሞቱ፥ ስለ ዕድሜው ማጠርም አይጨነቅም፤ ነገር ግን ከወርቅ ሠሪዎችና ክብር አቅላጮች ጋር ይፎካከራል፤ የነሐስ ሠራተኞችን ለመምሰል ይጥራል፤ አስመስሎ በመሥራቱም ይታበያል። 10 ልቡ አመድ፥ ተስፋው ከምድር የከፋ፥ ሕይወቱ ከጭቃ ይልቅ የተናቀ ነው። 11 ሕያው ነፍስ እፍ ያለበትን፥ የማይሞት መንፈስ የሰጠውን፥ አንዱን ፈጣሪውን ዘንግቷል። 12 ከዚህም በላይ ሸክላ ሠሪው ሕይወታችንን የሚያያት እንደ ጨዋታ ነው፤ ምድራዊ ቆይታችንንም ውጣ ውረድ እንደሚበዛበት ትርዕይት ይቆጥረዋል። 13 እርሱ ከማንም የበለጠ መበደሉን ራሱ ያውቀዋል፥ ከአንድ ዓይነት አፈር ተሰባሪ ሸክላና ጣኦቶችን የሚሠራ ነውና። የግብጻውያን ታላቅ ስሕተት፥ ገደብ የለሹ አምልኮተ ጣዖት 14 የመጨረሻዎቹ ሞኞች ከሕጻን ልጅ ነፍስም በበለጠ ሊታዘንላቸው የሚገቡ፥ የሕዝብ ጠላቶችና ባንድ ወቅት በአምባገነንነት ይጨቁናቸው የነበሩት ናቸው። 15 የአረማውያኑን ጣእቶች ሁሉ አማልክቶቻቸው አደጉ፤ እነርሱ ለማየት ዓይናቸውን፥ ለመተንፈስ አፍንጫቸውን፥ ለመስማት ጆሮዋቸውን፥ ለመጨበጥ ጣቶቻቸውን፥ ለመራመድም እግሮቻቸውን መጠቀም አይትሉም። 16 ጣኦቶቹ የተሠሩት በሰው፥ እስትንፋሱን በውሰት ባገኘ ፍጡር ነው። ማንም ሰው ራሱን የመሰለ ጣኦት ከቶ ሊቀርጽ አይችልም። 17 ሞት ዕጣ ፈንታው ነውና ያልተባረኩት እጆቹ ሊሠሩ የሚችሉት በድን ብቻ ነው። ከሚያመልካቸው ጣኦቶች ይልቅ፥ እርሱ የከበረ ነው፤ እርሱ መኖር ይችላል፥ እነርሱ ግን ፈጽሞ ሊኖሩ አይችሉም። 18 እጅግ የሚያስቀይሙትን እንስሳት ያመልካሉ፤ አእምሮ ቢስነታቸውም ከሌሎቹ ሁሉ የባሰ ነው። 19 እንስሳትን ተወዳጅ የሚያደርጋቸው ውበታቸው ከሆነ፥ ከቶውንም የማይስቡ የእግዚአብሔርን ቡራኬና ምርቃትም ያላኙ ናቸው። |