የሚወዱትን ሰው ማጣት በጣም ከባድ ነው። በዚህ ጊዜ ሀዘንና መከፋት ተፈጥሯዊ ነው። ስሜቱን ተረድቼዋለሁ። ግን ለሀዘኑ ብዙ ጊዜ አትስጡት። አብረናችን የሚኖረው አጽናኝ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዳለን አንዘንጋ። ሀዘናችንን ያስታግሳል፤ ጥንካሬና ብርታት ይሰጠናል። እኛ አማኞች ይህችን ምድር ስንለቅ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደተሻለ ቦታ እንደምንሄድ እናውቃለን። ከመድረሳችን በፊት ብዙ የምንወዳቸው ሰዎች እንደሚቀድሙን እናውቃለን። ነፍሳቸው ድና እንደሆነች ማወቅ ሊያስደስተን ይገባል፤ በተሻለ ቦታ እንዳሉ እናስብ።
ለእግዚአብሔር ነው የተፈጠርነው። ቃሉ እንዲህ ይላል፡- «ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ እንግዲህ ብንኖር ብንሞትም የጌታ ነን።» ስለዚህ ያንን መጽናናት ከእግዚአብሔር ፈልጉ፤ በእርሱ ታመኑ። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ እና ሊያበረታችሁ፣ ነፍሳችሁን ሊያሳርፍ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ሁኑ። እግዚአብሔር በሕይወታችሁ ውስጥ እንዲሠራ ፍቀዱለት። (ዮሐንስ 11:25) «ኢየሱስም፦ እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል» አላት።
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው።
እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣
ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤
ይህም እኔ በእነርሱ፣ አንተም በእኔ መሆንህ ነው። አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድኸኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድሃቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ፣ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን።
የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ።
እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ።
የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።
ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣
ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በርሱ ይኖራል።
ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤ በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው።
ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣ ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ።
በክፉ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ።
እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል።
የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል።
እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።
ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።
በዚያ ጊዜ ሞገስንና ማስተዋልን፣ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወድዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ ነው።
ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣
በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።
ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣
የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋራ የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው።
እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤
ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም።
ፍቅር ከእውነት ጋራ እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም።
ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።