የጋኔኑ ከሣራ መውጣት1 ተመግበውም በጨረሱ ጊዜ ጦብያን ወደ እርሷ አገቡት። 2 ወደ እርሷም በገባ ጊዜ የሩፋኤልን ነገር አሰበ፤ የዕጣን ዕራሪ ወሰደ፤ ከዚያም ዓሣ ከልቡና ከጉበቱ ጨምሮ አጤሰው። 3 ሽታውም ያን ጋኔን በሸተተው ጊዜ እስከ ላይኛው ግብፅ አውራጃ ድረስ ሸሸ። ያም መልአክ ጋኔኑን አሰረው። የጦብያ ጸሎት4 ሁለቱም በተዘጋባቸው ጊዜ ጦብያ ከአልጋው ተነሥቶ፥ “እኅቴ ተነሽ፤ እግዚአብሔር ይቅር ይለን ዘንድ እንጸልይ” አላት። 5 ጦብያም እንዲህ ይል ጀመረ፥ “አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ቅዱስ ስምህም ይባረክ፤ ለዘለዓለሙም ይመሰገናል። ሰማያትና የፈጠርሃቸው ሁሉ ያመሰግኑሃል። 6 አንተ አባታችን አዳምን ፈጠርኸው፤ ትረዳውና ታሳርፈውም ዘንድ ሔዋንን ሰጠኸው፤ ከእነዚያም የሰው ዘር ተወለደ፤ አንተም አልህ፦ ‘ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የሚረዳውን እንፍጠርለት።’ 7 አሁንም ይህቺን እኅቴን የማገባት በሚገባ ነው እንጂ ስለ ዝሙት አይደለምና አቤቱ አብረን ወደ ሽምግልና እንድንደርስ እንረዳዳ ዘንድ ለእኔና ለእርሷ ይቅርታን ላክልን።” 8 እርሷም ከእርሱ ጋር “አሜን” አለች። 9 ሁለቱም በዚያች ሌሊት አብረው አደሩ። 10 ከዚህም በኋላ ራጉኤል ተነሥቶ ሄደ፤ እርሱም “ምናልባት ይሞት ይሆናል” ብሎ መቃብር ቈፈረ። 11 ራጉኤልም ወደ ቤቱ ተመለሰ። 12 ሚስቱ አድናንም አላት፥ “ደኅና እንደ ሆነ ታየው ዘንድ አንዲት ልጅ ላኪ፤ ሞቶም እንደ ሆነ ማንም ሳያውቅ እንቀብረዋለን።” 13 ያቺም ልጅ ሄዳ ደጃፉን ከፈተች፤ ሁለቱም ተኝተው አገኘቻቸው። 14 ተመልሳም እርሱ ደኅና እንደ ሆነ ነገረቻቸው። 15 ራጉኤልም እግዚአብሔርን አመሰገነው፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ አንተ የተመሰገንህ ነህ፤ ንጽሕትና ቅድስት በሆነች ምስጋና ሁሉ የተመሰገንህ ነህ። ጻድቃንህ፦ በሠራኸው ሥራ ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ መላእክትህና የመረጥኻቸውም ሁሉ ለዘለዓለም ያመሰግኑሃል። 16 ደስ አሰኝተኸኛልና አቤቱ አንተ የተመሰገንህ ነህ፤ እንደ ጠረጠርሁት አልተደረገብኝም፤ ነገር ግን እንደ ቸርነትህ ብዛት አደረግህልኝ። 17 አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሁለቱን ብቸኞች ይቅር ብለሃቸዋልና፥ ዘመናቸውን በደኅንነትና በደስታ፥ በቸርነትህ ይፈጽሙ ዘንድ አቤቱ በጎነትን አድርገህላቸዋልና።” 18 ከዚያም በኋላ ራጉኤል ያን መቃብር ይደፍኑ ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው። የሰርጉ በዓል19 ከዚህም በኋላ ዐሥራ አራት ቀን በዓል አደረገላቸው። 20 ራጉኤልም የሠርጉ ዐሥራ አራት የበዓል ቀን እስኪፈጸም ድረስ ወጥቶ እንዳይሄድ ጦብያን አማለው። 21 ከዚህም በኋላ ሄዶ የገንዘቡን እኩሌታ ይወስድ ዘንድ፥ ወደ አባቱም በደኅና ይሄድ ዘንድ፥ የተረፈውን ግን እርሱና ሚስቱ ከሞቱ በኋላ ይወስድ ዘንድ አስማለው። |