የጦብያ ወላጆች እንደ ተጨነቁ1 አባቱ ጦቢት ግን ቀኑን ይቈጥር ነበር። ቀጠሮውም አልቆ ሳይመጡ በቀሩ ጊዜ፥ 2 እንዲህ አለ፥ “ምናልባት እነሆ፥ ልጄ ታስሮ ይሆን? ወይስ ገባኤል ሞቶ ብሩን የሚሰጠው አላገኘ ይሆን?” 3 እጅግም አዘነ። 4 ሚስቱም፥ “ልጄስ ሞትዋል፤ ስለዚህም ነገር ዘገየ” አለችው። 5 እንዲህም እያለች ታለቅስ ጀመረች፤ “ያይኔን ብርሃን ልጄን ያጠፋህብኝ ባይሆን ባላሳዘነኝም ነበር።” 6 እርሱም፥ “ዝም በዪ፤ አትጨነቂ፤ እርሱስ ደኅና ነው” አላት። 7 እርሷም አለችው፥ “አንተም ዝም በል፤ አታታለኝ፤ ልጄስ ሞትዋል።” ታለቅስለትም ዘንድ በሄደበት ጎዳና ሁልጊዜ ትሄድ ነበር። የሰርጉ በዓል ሳያልቅ እንዳይሄድ ራጉኤል ያማለው ዐሥራ አራቱ የበዐዓል ቀን እስኪፈጸም ድረስ ለልጅዋ ለጦብያ እያለቀሰችለት በቀን እህል አትበላም ነበር፤ በሌሊትም ዝም አትልም ነበር። የጦብያና ሣራ ወደ ቤታቸው መመለስ8 ከዚህ በኋላ የሰርጉ በዐል ባለቀ ጊዜ ጦብያ ራጉኤልን አለው፥ “እንግዲህስ ወዲያ አሰናብተኝ፤ አባቴና እናቴ ተስፋ ቈርጠዋልና እንግዲህ ወዲህም ያዩኝ ዘንድ ተስፋ አያደርጉምና፥” 9 አማቱም፥ “በእኔ ዘንድ ተቀመጥ፤ ወሬህን ይነግሩት ዘንድ እኔ ወደ አባትህ እልካለሁ” አለው። 10 ጦብያም፥ “አይሆንም፥ ወደ አባቴ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ እንጂ” አለው። 11 ራጉኤልም ተነሥቶ ሚስቱ ሣራንና፥ የገንዘቡን እኩሌታ፥ አገልጋዮችን፥ ከብቶችንም፥ ብሩንም ሰጠው። 12 እርሱም፥ “ልጆች ሆይ፥ ሳልሞት የሰማይ ጌታ በጎ ነገር ያድርግላችሁ” ብሎ መረቃቸው፤ ልጁንም እንዲህ አላት፥ “አማቶችሽን አክብሪ፤ እንግዲህ ወዲህ ዘመዶችሽ እነርሱ ናቸውና፤ እኛም በአንቺ መልካሙን እንስማ” ብሎ ሳማት። አድናም ጦብያን አለችው፥ “አንተ የምወድህ ወንድሜ ሆይ፥ የሰማይ ጌታ ከልጄ ከሣራ ልጆችን ሰጥቶህ አይልህ ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ደስ ይለኝ ዘንድ ጎዳናህን ያቅናልህ። እነሆ፥ ልጄን አደራ ሰጥቼሃለሁ፤ አታሳዝናት።” 13 ከዚህም በኋላ ጦብያ ሄደ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነው፤ መንገዱን አቅንቶለታልና። ራጉኤልና ሚስቱ አድናም አመሰገኑት፤ እነርሱም ሄዱ፤ ወደ ነነዌም ቀረቡ። |