1 ነገሥት 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰማርያ በሶርያ ጦር እንደ ተከበበች (በዕብ. ምዕ. 20 ነው።) 1 የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት፤ እየጠበቃቸውም ተቀመጠ። ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ነበሩ፤ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፤ ወጥተውም ሰማርያን ከበቧት፥ ወጓትም። 2 ወደ ከተማው ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ እንዲህ ብሎ ላከ፦ 3 “ወልደ አዴር እንዲህ ይላል፦ ብርህና ወርቅህ የእኔ ነው፤ ሚስቶችህና ልጆችህም የእኔ ናቸው።” 4 ንጉሡ አክዓብም መልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ! አንተ እንዳልህ፤ እኔ የአንተ ነኝ፤ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” አለ። 5 ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው መጥተው እንዲህ አሉት፥ “ወልደ አዴር እንዲህ ይላል፦ ቀድመህ ብርህንና ወርቅህን፥ ሚስቶችህንና ልጆችህንም ላክልኝ ብዬ ልኬብህ ነበር፤ 6 ይህ ካልሆነ ነገ በዚህ ጊዜ አገልጋዮቼን እልክብሃለሁ፤ ቤትህንም፥ የአገልጋዮችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ ለዐይናቸው ደስ ያሰኛቸውን ሁሉና በእጃቸው የዳሰሱትንም ሁሉ ይወስዳሉ።” 7 የእስራኤልም ንጉሥ የሀገሩን አለቆች ሁሉ ጠርቶ፥ “ተመልከቱ፤ ይህም ሰው ክፉ እንዲሻ እዩ፤ ስለ ሚስቶቼ ስለ ወንዶች ልጆቼና ሴቶች ልጆቼ ላከብኝ፤ ብሬንና ወርቄን ግን አልከለከልሁትም” አላቸው። 8 አለቆችና ሕዝቡም ሁሉ፥ “እንቢ በለው፤ እሺም አትበለው” አሉት። 9 ለወልደ አዴር መልእክተኞችም፥ “ለጌታችሁ፦ ለእኔ አገልጋይህ በመጀመሪያ የላክህብኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ይህን ነገር ግን አደርገው ዘንድ አይቻለኝም” በሉት አላቸው። መልክእክተኞችም ተመልሰው ይህን ነገር ነገሩት። 10 ዳግመኛም ወልደ አዴር እንዲህ ብሎ ወደ እርሱ ላከ፥ “ሕዝቤና ሠራዊቴ ሁሉ ሀገርህን ሰማርያን ባያጠፉት፥ የቀበሮም ማደሪያ ባያደርጉት አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ እንዲህም ይግደሉኝ።” 11 የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፥ “ይሁን፤ ይህ ጐባጣ እንደ ቀና አይመካ” ብሎ መለሰ። 12 ከዚህም በኋላ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ አብረውት ካሉት ከነገሥታቱ ሁሉ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ አገልጋዮቹንም፥ “ከተማውን እጠሩት” አላቸው። እነርሱም በከተማዪቱ ትይዩ ተሰለፉ። 13 እነሆም፥ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ መጥቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ብዙ ሕዝብ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እንግዲህ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ” አለው። 14 አክዓብም፥ “በምን አውቃለሁ?” አለ፤ እርሱም፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአውራጃዎቹ አለቆች ጐልማሶች” አለ፤ አክዓብም፥ “ውጊያውን ማን ይጀምራል?” አለ፤ እርሱም፥ “አንተ” አለው። 15 አክዓብም የአውራጃዎቹን አለቆች ጐልማሶች ቈጠረ፤ ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለትም ሆኑ፤ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእራኤልን ልጆች ሁሉ ቈጠረ፤ ሰባት ሺህም ሆኑ። 16 ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፤ ወልደ አዴርም በማቅ ድንኳን ውስጥ ጠጥቶ ሰክሮ ነበረ፤ የሚረዱት ሠላሳ ሁለት ነገሥታትም አብረውት ነበሩ። 17 የአውራጃዎቹም አለቆች ጐልማሶች አስቀድመው መጥተው ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር፥ “እነሆ፥ ሰዎች ከሰማርያ መጡ” ብለው ነገሩት። 18 እርሱም፥ “ለሰላም መጥተው እንደ ሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው፤ ለውጊያ መጥተው እንደ ሆነ ግን ተዋጓቸው” አለ። 19 እነዚህም የአውራጃዎች አለቆች ጐልማሶች ከከተማዪቱ ወጡ፤ ሠራዊትም ተከተላቸው። 20 ሁሉም እያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፤ ደጋግመውም ገደሉ። ከዚህም በኋላ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፤ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴርም በፈጣን ፈረስ አመለጠ። 21 የእስራኤልም ንጉሥ ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፤ ሶርያውያንንም በታላቅ አገዳደል ገደላቸው። 22 አንድ ነቢይም ወደ እስራኤል ንጉሥ መጥቶ፥ “የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና፥ በርታ፤ የምታደርገውንም ዕወቅ” አለው። 23 የሶርያም ንጉሥ አገልጋዮች እንዲህ አሉት፥ “የእስራኤል አምላክ የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፤ ነገር ግን በሜዳ ብንዋጋቸው ድል እናደርጋቸው ነበር። 24 ይህንም የምነግርህን ነገር አድርግ፤ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ዘንድ እኒህን ነገሥታት አሰናብታቸው፤ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም። 25 ሌሎች ሠራዊትን እናመጣልሃለን፤ አንተም ቀድሞ በሞቱብህ ሠራዊት ምትክ ሹም፤ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሰረገላውን በሰረገላ ፋንታ ለውጥ፤ በሜዳውም እንዋጋቸዋለን፤ ድልም እናደርጋቸዋለን።” እርሱም ምክራቸውን ሰማ፤ እንዲሁም አደረገ። 26 ከዚህም በኋላ በዓመቱ ወልደ አዴር ሶርያውያንን ቈጠራቸው፤ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ። 27 የእስራኤልም ልጆች ተቈጠሩ፤ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሽ የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፤ ሶርያውያን ግን ምድርን ሞልተዋት ነበር። 28 የእግዚአብሔርም ሰው መጥቶ የእስራኤልን ንጉሥ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሶርያውያን፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ሠራዊት ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ” አለው። 29 እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፤ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ። 30 የቀሩትም ወደ አፌቅ ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ሸሹ፤ ቅጥሩም በቀሩት በሃያ ሰባት ሺህ ሰዎች ላይ ወደቀ። ወልደ አዴርም ሸሽቶ ወደ ከተማዪቱ ወደ እልፍኙ ውስጥ ገባ። 31 እርሱም ለአገልጋዮቹ፥ “እነሆ፥ የእስራኤል ነገሥታት መሓሪዎች ነገሥታት እንደ ሆኑ አውቃለሁ፤ በወገባችን ማቅ እንታጠቅ፤ በራሳችንም ገመድ እንጠምጥም፤ ወደ እስራኤልም ንጉሥ እንሂድ፤ ምናልባት ሰውነታችንን ያድናት ይሆናል” አላቸው። 32 ወገባቸውንም በማቅ ታጠቁ፤ በራሳቸውም ገመድ ጠመጠሙ፤ ወደ እስራኤልም ንጉሥ ገብተው፥ “ባሪያህ ወልደ አዴር፦ ሰውነታችንን አድነን አለህ” አሉት። እርሱም፥ “ገና በሕይወት አለን? ወንድሜ ነው” አለ። 33 ሰዎቹም የደግ ምልክት አደረጉትና ቃሉን ከአፉ ተቀብለው፥ “ወንድምህ ወልደ አዴር አለ” አሉት። እርሱም፥ “ሂዱና አምጡት” አለ። ወልደ አዴርም ወደ እርሱ መጣ፤ በሰረገላውም ላይ አስቀመጠው። 34 ወልደ አዴርም፥ “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገ አንተም በደማስቆ መንገድ ታደርጋለህ” አለው። አክዓብም፥ “እኔም በዚህ ቃል ኪዳን እሰድድሃለሁ” አለ። ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን አድርጎ ሰደደው። 35 ከነቢያትም ልጆች አንድ ሰው መጥቶ በእግዚአብሔር ቃል ባልንጀራውን፥ “ግደለኝ” አለው። ሰውዬውም ይገድለው ዘንድ እንቢ አለ። 36 እርሱም፥ “የእግዚአብሔርን ቃል መስማት እንቢ ብለሃልና እነሆ፥ ከእኔ ተለይተህ በሄድህ ጊዜ አንበሳ ይገድልሃል” አለው። ከእርሱም ተለይቶ በሄደ ጊዜ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። 37 ደግሞም ሌላ ሰው አግኝቶ፥ “ግደለኝ” አለው። ሰውዬውም መታው በመምታቱም አቈሰለው። 38 ነቢዩም ሄዶ በመንገድ አጠገብ ንጉሡን ጠበቀው፤ ዐይኖቹንም በቀጸላው ሸፈነ። 39 ንጉሡም ባለፈ ጊዜ ወደ እርሱ ጮኸ፥ “ባሪያህ ወደ ሰልፍ መካከል ወጣ፤ እነሆም፥ አንድ ሰው ፈቀቅ ብሎ ወደ እኔ መጣ፤ አንድ ሰውም አመጣና፦ ይህን ሰው ጠብቅ፤ ቢኰበልልም ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ትሆናለች፤ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ አለኝ። 40 ከዚህም በኋላ አገልጋይህ ወዲህና ወዲያ ሲመለከት ጠፋ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ፥ “ፍርድህ እንዲሁ ይሆናል፤ አንተ ፈርደኸዋል” አለው። 41 ፈጥኖም ቀጸላውን ከዐይኑ አነሣ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያት ወገን እንደ ሆነ ዐወቀው። 42 ያም ነቢይ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ እርም ያልሁትን፥ ሞትም የሚገባውን ሰው ከእጅህ አውጥተሃልና፥ ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ፥ ሕዝብህም በሕዝቡ ፋንታ ይሆናሉ” አለው። 43 የእስራኤልም ንጉሥ አዝኖና ተክዞ ወደ ሰማርያ ሄደ። |