1 “አቤቱ! ነግሠህ የምትኖር የእስራኤል አምላክ ሆይ! የተራበች ነፍስ፥ ያዘነችም ነፍስ ወደ አንተ ጮኸች። 2 አቤቱ! ሰምተህ ይቅር በላት፤ በፊትህ በድለናልና። 3 አንተ ለዘለዓለሙ የምትኖር ነህና፥ እኛ ግን ለዘለዓለሙ እንጠፋለንና። 4 በሁሉ ላይ የምትነግሥ የእስራኤል አምላክ አቤቱ! የሙታን የእስራኤልን፥ በፊትህም የበደሉ፥ የአምላካቸውንም ቃል ያልሰሙ የልጆቻቸውን ጸሎት ስማ። 5 ክፉ ነገርም ተከተለን፤ የአባቶቻችንንም ኀጢአት አላሰብንም፤ በዚህም ወራት እጅህንና ስምህን ዐስብ። 6 አንተ እግዚአብሔር አምላካችን ነህና አቤቱ! እናመሰግንሃለን። 7 ስለዚህም ስምህን እንጠራ ዘንድ፥ ባስማረክኸንም ቦታ እናመሰግንህ ዘንድ መፈራትህን በልቡናችን አሳደርህ። በፊትህ የበደሉ የአባቶቻችንን ክፋት ሁሉ ከልባችን አርቀናልና። 8 አቤቱ አምላካችን! እነሆ ዛሬ፦ ከአንተ እንደ ራቁ አባቶቻችን ክፋት ሁሉ ለውርደት፥ ለርግማንና ለፍዳ በበተንኸን ምርኮ ውስጥ ነን።” 9 እስራኤል ሆይ፥ የሕይወትን ትእዛዝ ስማ፥ የጥበብንም ምክር አድምጥ። 10 እስራኤል ምንድን ነው? በጠላትስ ሀገር ለምን ይኖራል? 11 በባዕድ ሀገርስ ለምን ጠፋ? ከሬሳዎችስ ጋር ለምን ረከሰ? ወደ መቃብር ከወረዱት ጋርስ ለምን ተቈጠረ? 12 የሕይወትን ምንጭ ተውህ? 13 በእግዚአብሔርስ መንገድ ብትሄድ ለዘለዓለም በሰላም በኖርህ ነበር! 14 ተማር፥ ጥበብ ከየት ነው? ኀይልስ ከየት ነው? ምክርና ዕውቀትስ ከየት ናቸው? ለብዙ ዘመናት መኖርስ ከየት ነው? የዐይኖች ብርሃንና ሰላም ከየት ናቸው? 15 የጥበብ ሀገሯን ማን አገኘ? ወደ መዛግብትዋስ ማን ገባ? 16 የምድረ በዳ አውሬዎችን የገዙ የአሕዛብ አለቆች ወዴት ናቸው? 17 በሰማይ አዕዋፍም የሚጫወቱ ሰዎች የሚታመኑበት ብርና ወርቅን የሚሰበስቡ፤ ለመሰብሰባቸውም ወሰን የሌላቸው የአሕዛብ አለቆች ወዴት ናቸው? 18 ብርን የሚያነጥሩ ይተጋሉና፥ ለሥራቸውም ምርመራ የለውም። 19 አለቁ፤ ወደ መቃብርም ወረዱ፤ ስለ እነርሱም ሌሎች ተተኩ። 20 ታናናሾች ብርሃንን አዩ፤ በምድራቸውም ኖሩ፤ የጥበብን መንገድ ግን አላወቁም። 21 ፍለጋውንም አላገኙም፤ አልተቀበሉአትም፤ ልጆቻቸውም ከመንገዳቸው ራቁ። 22 የከነዓን ሰዎች አልሰሙም፤ የቴምናም ሰዎች አላዩም። 23 በምድር ጥበብን የሚፈልጓት የአጋር ልጆችም የሚጫወቱባት፥ ዕውቀትንም የሚፈልጓት፥ የመርያንና የቴምና ነጋዴዎችም የጥበብን ጐዳና አላወቁም፤ ፍለጋዋንም አላስተዋሉም። 24 እስራኤል ሆይ! የእግዚአብሔር ቤት እንዴት ታላቅ ነው! ቦታውም እንዴት ሰፊ ነው! ፍጻሜ የለውም፤ መለኪያም የለውም። 25 ታላቅ ነው፤ ፍጻሜም የለውም፤ ላይኛውም መለኪያ የለውም። 26 ከጥንት ጀምሮ ቁመታቸው ረዥም የሆነ፥ ጦርነትንም የሚያውቁ ረዐይት የሚባሉ በዚያ ነበሩ። 27 እነዚህን እግዚአብሔር አልመረጣቸውም፤ የዕውቀት መንገድንም አልሰጣቸውም። 28 ጥበብ አልነበራቸውምና ጠፉ፤ በድፍረታቸውም ጠፉ። 29 ወደ ሰማይ የወጣና የያዛት፤ ከደመናትም ያወረዳት ማነው? 30 ባሕሩን ተሻግሮ ያገኛት፥ በቀይ ወርቅስ ያመጣት ማነው? 31 መንገድዋን የሚያውቅ፥ ፍለጋዋንም የሚያስብ የለም። 32 ሁሉን የሚያውቅ ያውቃታል፤ በጥበቡም አገኛት። ምድርን የፈጠረ ለዘለዓለም በእንስሳት ሞላት። 33 ብርሃኑን ይልካል፤ እርሱም ይሄዳል፤ እንደ ገናም ይጠራዋል፤ በፍርሃትም ይታዘዘዋል። 34 ከዋክብትም በየጊዜያቸው ያበራሉ፤ ደስም ይላቸዋል። 35 ይጠራቸዋል፤ እነርሱም፦ መጣን ይላሉ። ለፈጠራቸውም በደስታ ያበራሉ። 36 እርሱን የሚመስል ሌላ የለምና አምላካችን ነው ይላሉ። 37 የጥበብን መንገድ ሁሉ እርሱ አገኛት፤ ለባለሟሉ ለያዕቆብ፥ ለወዳጁም ለእስራኤል ሰጠው። 38 ከዚህ በኋላ በምድር ተገለጠ፤ እንደ ሰውም ሆነ። |