Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ባሮክ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “አምላካችን በእኛና እስራኤልን በገዙ መሳፍንቶቻችን ላይ፥ በነገሥታቶቻችን ላይና በመኳንንቶቻችን ላይ፥ በይሁዳና በእስራኤልም ሁሉ ላይ የተናገረውን ቃሉን አጸና። 2 በሙሴ ኦሪት እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም እንደ አደረገው ከሰማይ በታች ያልሆነ ክፉ ነገርን በእኛ ላይ ያመጣ ዘንድ፥ ቃሉን አጸና። 3 በዚያ ወራት ሰው የወንዶች ልጆቹንና የሴቶች ልጆቹን ሥጋ በላ። 4 እግዚአብሔር እነርሱን በበተነበት በዙሪአችን በአሉ አሕዛብ ዘንድ ለውርደትና ለመከራ ይሆኑ ዘንድ በዙሪያችን በአሉ ነገሥት ሁሉ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 5 ወራዶች ሆንን፤ የከበርንም አልሆንም፤ ለቃሉ ሳንታዘዝ አምላካችንን እግዚአብሔርን በድለናልና። 6 ጽድቅ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ ለእኛና ለአባቶቻችን ግን እንደ ዛሬው ዕለት የፊት ኀፍረት ነው። 7 በእኛ ላይ የደረሰውን ክፉ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ተናግሮ ነበርና። 8 እያንዳንዳችንም ከክፉ ልባችን መንገድ እንመለስ ዘንድ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት አልጸለይንም። 9 እግዚአብሔርም ለመከራ ተጋ፤ በእኛም ላይ አመጣው፤ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ባዘዘው ሥራው ሁሉ ጻድቅ ነውና። 10 በፊታችን በሰጠን በእግዚአብሔርም ትእዛዝ እንሄድ ዘንድ ቃሉን አልሰማንም። 11 “አሁንም በጸናች እጅ፥ በተአምርና በድንቅ ሥራ፤ በታላቅ ኀይልና በተዘጋጀች ክንድ ሕዝብህን ከግብፅ ምድር ያወጣህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው ለራስህ ታላቅ ስምን ያደረግህ የእስራኤል አምላክ ሆይ! 12 በደልን፤ ክፉም አደረግን፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ! በሥርዐትህ ሁሉ ላይ የማይገባ ሥራን ሠራን። 13 ቍጣህን ከእኛ አብርድ፤ እኛን በዚያ በበተንህበት በአሕዛብ ዘንድ ጥቂት ቀርተናልና። 14 ጌታ ሆይ! ልመናችንንና ጸሎታችንን ስማ፤ ስለ ስምህም ስትል አድነን፤ በማረኩንም ሰዎች ፊት ሞገስን እናገኝ ዘንድ ስጠን፤ 15 ምድር ሁሉ አንተ እግዚአብሔር አምላካችን እንደ ሆንህ ታውቅ ዘንድ፥ ስምህ በእስራኤል ላይና በወገኑ ላይ ተጠርቶአልና ። 16 አቤቱ ከቤተ መቅደስህ ሁነህ ተመልከት፤ አቤቱ ጆሮህን ወደ እኛ አዘንብለህ ስማን። 17 “ዐይኖችህን ገልጠህ ተመልከት፤ አቤቱ ነፍሳቸው ከሥጋቸው የተለየች በመቃብር የሚኖሩ ሙታን የሚያከብሩህና የሚያመሰግኑህ አይደሉምና። 18 ነገር ግን አዝናና ተጨንቃ የምትኖር፥ በብዙ መከራም ያዘነች ሰውነትና የፈዘዙ ዐይኖች፥ የተራበችም ነፍስ ያመሰግኑሃል፤ አቤቱ ለጽድቅህም ይገዛሉ። 19 አቤቱ አምላካችን በፊትህ ምሕረትን የለመንንህ እንደ አባቶቻችንና ነገሥታቶቻችን ጽድቅ አይደለምና። 20 በባሪያዎችህ በነቢያት እጅ እንደ ተናገርህ መዓትህንና መቅሠፍትህን በእኛ ላይ ሰድደሃልና። 21 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትከሻችሁን ዝቅ አድርጉ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፤ ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድርም ትኖራላችሁ፤ 22 የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ ለባቢሎንም ንጉሥ ባትገዙ፥ 23 የደስታና የሐሤት ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራና የሴት ሙሽራ ድምፅ ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋል፤ ምድርም ሁሉ ከነዋሪዎች ምድረ በዳ ይሆናል። 24 ቃልህን አልሰማንም፤ ለባቢሎንም ንጉሥ አልተገዛንም፤ የንጉሦቻችን ዐፅሞችና የአባቶቻችን ዐፅሞች ከቦታቸው እንደሚወጡ በባሮችህ ነቢያት እጅ የተናገርኸውም ደረሰብን። 25 “እነሆ በቀን ሐሩርና በሌሊት ቍር ጣሏቸው፤ ተማረክን፤ በቀጠናና በጦር፥ በቸነፈርም ክፉ ሞትን ሞትን። 26 በእስራኤል ወገንና በይሁዳ ወገን ኀጢአት ምክንያት ስምህ የተጠራበትን መቅደስ እንደ ዛሬው ዕለት ጣልህ። 27 ነገር ግን አቤቱ አምላካችን! እንደ ቸርነትህ ሁሉና እንደ ታላቁ ይቅርታህ ሁሉ አደረግህልን፤ 28 በእስራኤል ልጆች ፊት ሕግህን ይጽፍ ዘንድ ባዘዝህባት ዕለት በአገልጋይህ በሙሴ እጅ እንዲህ ስትል እንደ ተናገርህ፥ 29 ቃሌን በእውነት ባትሰሙ ይህች ብዛታችሁ እናንተን በበተንሁባቸው በአሕዛብ መካከል ወደ ጥቂትነት ትመለሳለች። 30 “እንደማይሰሙኝም ዐወቅኋቸው፤ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናቸውና፤ በተሰደዱበትም ሀገር ወደ ፈቃዳቸው ይመለሳሉ። 31 እኔም አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። ልብን፥ ለመስማትም ጆሮን እሰጣቸዋለሁ። 32 ባስማረክኋቸውም ሀገር ያመሰግኑኛል፤ ስሜንም ያስባሉ። 33 ከደንዳና ልባቸውና ከክፉ ሥራቸው ይመለሳሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት የበደሉ የአባቶቻቸውንም መንገድ ያስባሉ። 34 ለአባቶቻቸው ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብም ወደ ማልሁላቸው ሀገር እመልሳቸዋለሁ፤ ይገዙአታልም፤ እኔም አበዛቸዋለሁ፤ እነርሱም አያንሱም። 35 አምላካቸው እሆናቸው ዘንድ የዘለዓለም ቃል ኪዳንን እሠራላቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ሕዝቤ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ሀገራቸው አላወጣቸውም። |