Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ባሮክ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የዘላለም ሕግ የሆነ የእግዚአብሔር የትእዛዙ መጽሐፍ ይህ ነው፤ የሚጠብቋትም ሁሉ ይኖራሉ፤ የሚተዉኣት ግን ይሞታሉ። 2 ያዕቆብ! ተመልሰህ ያዛት፤ በብርሃንዋም ሂድ። 3 ክብርህን ለባዕድ አትስጥ፤ የሚሻልህንም ለሌላ ወገን አትስጥ። 4 የአምላካችን የእግዚአብሔር ምሕረት በእኛ ታውቋልና እኛ እስራኤል ብፁዓን ነን። መጽናናት ለእስራኤል 5 ወገኖች ተጽናኑ፤ እስራኤልም አስቡ። 6 ለጥፋት ያይደለ ለሌላ ወገን ተሽጣችሁ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ስላስቈጣችሁት ለጠላቶቻችሁ ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ ነበር። 7 ለእግዚአብሔር ያይደለ ለአጋንንት በመሠዋታችሁ ፈጣሪያችሁን ለመዓት አነሳሳችሁት። 8 ያሳደጋችሁን የዘለዓለም አምላካችሁንም ረስታችሁታልና፥ ሞግዚታችሁን ኢየሩሳሌምንም አሳዝናችኋታልና። 9 የመጣባችሁን የእግዚአብሔርን መቅሠፍት ባየች ጊዜ እንዲህ አለች፦ የጽዮን ስደተኞች ስሙ፤ እግዚአብሔር ጽኑፅ ልቅሶን አምጥቶብኛልና። 10 ዘለዓለማዊ አምላክ ያመጣባቸውን የወንዶች ልጆችንና የሴቶች ልጆችን መማረክ አይቻለሁና 11 በደስታ አሳድጊያቸው ነበር፤ ነገር ግን በልቅሶና በኀዘን ሸኘኋቸው። 12 በብዙዎች ዘንድ የተጣልሁ በሆንሁ በእኔ በመበለቲቱ ደስ የሚለው አይኑር፤ ከእግዚአብሔር ሕግ ርቀዋልና። 13 ትእዛዙንም አላወቋትም፤ በእግዚአብሔርም በትእዛዙ መንገድ አልተመላለሱም፤ በምክሩም ፍለጋ ወደ ጽድቁ አልገቡም። 14 የጽዮን ስደተኞች ይምጡ፤ ዘለዓለማዊው አምላክ ያመጣባቸውን የወንዶች ልጆችንና የሴቶች ልጆችንም ምርኮ ያስቡ። 15 የማያፍርና ቋንቋው ልዩ የሆነ ሕዝብን ከሩቅ አምጥቶባቸዋልና፤ ሽማግሌውን አላከበሩምና፥ ለሕፃናቱም አልራሩምና። 16 የመበለትነቷንም የተወደዱ ልጆች ነጠቁ፤ ከሴቶች ልጆችዋም ለይተው ብቻዋን አስቀሩአት። 17 ነገር ግን እኔ ምን ረዳችኋለሁ? 18 ክፉ ነገርን ያመጣባችሁ እርሱ ከጠላቶቻችሁ እጆች ያወጣችኋልና። 19 ልጆች! መንገዳችሁን ሂዱ፤ መንገዳችሁን ሂዱ፤ እኔ የተፈታች ምድረ በዳ ሁኛለሁና። 20 የሰላም ልብሴን አወለቅሁ፤ የመከራዬንም ማቅ ለበስሁ፤ በዘመኔም ወደ ዘለዓለማዊው አምላክ እጮሃለሁ፤ 21 ልጆች ተጽናኑ፤ ወደ አምላክም ጩኹ፤ ከጠላቶቻችሁ እጅና አገዛዝ ያወጣችኋል። 22 ከዘለዓለማዊው አምላክ ዘንድ ድኅነታችሁን ተስፋ አድርጌአለሁና። ከዘለዓለማዊው መድኀኒታችን ዘንድ ፈጥኖ ስለሚመጣላችሁ ምሕረትም ደስታ ከቅዱሱ መጣልኝ፤ 23 ከኀዘንና ከልቅሶ ጋር ሸኝቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እናንተን በደስታና በሐሤት ለዘለዓለም ይመልስልኛል። 24 የጽዮን ጎረቤቶች መማረካችሁን እንዳዩ፥ እንዲሁም በታላቅ ክብርና በዘለዓለማዊው አምላክ ብርሃን ከእግዚአብሔር ዘንድ የምትመጣላችሁን ድኅነታችሁን ፈጥነው ያያሉ። 25 ልጆች! ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣባችሁን ቍጣ በትዕግሥት ተቀበሉ፤ ጠላቶቻችሁ አሳድደዋችኋልና ውድቀታቸውን ፈጥናችሁ ታያላችሁ፤ በራሳቸውም ላይ ትወጣላችሁ። 26 ቅምጥሎች በሻካረው መንገድ ሄዱ፤ ጠላቶችም እንደ ተዘረፉ በጎች ነጠቋቸው። 27 ልጆች! ተጽናኑ፤ ወደ አምላክም ጩኹ፤ የወሰዳችሁ እርሱ ያስባችኋል። 28 ከእግዚአብሔር ትርቁ ዘንድ ፈቃዳችሁ እንደ ሆነ እንዲሁ ዐሥር ጊዜ ወደኋላ ተመልሳችሁ ትፈልጉታላችሁ፤ 29 ይህን መቅሠፍት ያመጣባችሁ እርሱ ዘለዓለማዊ ደስታን ከድኅነታችሁ ጋር ዳግመኛ ያመጣላችኋል። የኢየሩሳሌም ረድኤት እንደ ተረጋገጠ 30 ኢየሩሳሌም ተጽናኚ፤ ስም ያወጣልሽ እርሱ ያጽናናሻል። 31 መከራ ያጸኑብሽና በውድቀትሽም ደስ ያላቸው ይጐሰቍላሉ። 32 ልጆችሽን የገዙ፥ ልጆችሽንም ማርከው የወሰዱ ከተሞች ይጐሰቍላሉ። 33 በጥፋትሽ ደስ እንደ አላት፥ በውድቀትሽም ሐሤት እንደ አደረገች እንዲሁ በራስዋ ጥፋት ታዝናለች። 34 ብዙ ደስታዋንም ከእርስዋ አስወግዳለሁ፤ ደስታዋም ወደ ኀዘን ይመለሳል። 35 እሳት ከዘለዓለማዊው አምላክ ለረዥም ዘመን ይመጣባታልና ለብዙ ዘመንም የአጋንንት ማደሪያ ትሆናለችና። 36 ኢየሩሳሌም ወደ ምሥራቅ ተመልከች ከአምላክሽ ከእግዚአብሔር የመጣልሽ ደስታንም እዪ። 37 እነሆ የላክሻቸው ልጆችሽ መጡ፤ በቅዱሱም ቃል ከምሥራቅና ምዕራብ ተሰበሰቡ፤ በእግዚአብሔርም ክብር ደስ ይላቸዋል። |