የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደገና እንደ ተጀመረ1 በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመተ መንግሥቱ፦ ነቢያቱ ሐጌና የሐዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ባሉ አይሁድ ላይ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናገሩ። 2 ከዚህም በኋላ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኤዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ተነሡ፤ የእግዚአብሔርም ነቢያት እየረዱአቸው ከእነርሱ ጋር ሳሉ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ጀመሩ። 3 በእነዚያም ወራት የሶርያና የፊንቂስ ገዥ ሲሳኒስና ሳትራቡዛኒስ ከባልንጀሮቻቸው ጋር ወደ እነርሱ መጡ። 4 እንዲህም አሏቸው፥ “ይህን ቤትና ጣራውን፥ ሌላውንም ሥራ ሁሉ ትሠሩ ዘንድ ማን አዘዛችሁ? የሚሠሩትስ ግንበኞች እነማን ናቸው?” 5 ያንጊዜም እግዚአብሔር ይቅር ብሏቸዋልና ለአይሁድ ሽማግሌዎች ባለሟልነትን ሰጣቸው። 6 ወደ ዳርዮስ እስኪልኩ፥ ደብዳቤንም እስኪያመጡላቸው ድረስ ሥራውን አልከለከሏቸውም። 7 የሶርያና የፊንቂስ ገዥ ሲሳኒስና ሳትራቡዛኒስ፥ በሶርያና በፊንቂስም ከእነርሱ ጋር ያሉ ሹሞች፥ ባልንጀሮቻቸውም “ለንጉሡ ለዳርዮስ ትድረስ” ብለው ወደ ዳርዮስ ጽፈው ላኩ። 8 “ጌታችን ንጉሥ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን! ሁሉን እንድታውቅ ወደ ይሁዳ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣን ጊዜ የአይሁድ ምርኮኞች አለቆችን በኢየሩሳሌም ከተማ አገኘናቸው። 9 በተጠረበና ዋጋው ብዙ በሆነ ድንጋይ፥ በየወገናቸው ማዕዘን ባላቸው እንጨቶችም ታላቅና አዲስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቤት ሲሠሩ አገኘናቸው። 10 በችኰላም ይሠሩና ያፋጥኑ ነበር፤ በእጃቸውም እያስተካከሉ በትጋት ይሠሩ ነበር። በክብርና በጥንቃቄም ተሠራ። 11 ከዚህም በኋላ ‘ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንም መሠረት ትጥሉ ዘንድ ማን አዘዛችሁ?’ ብለን አለቆቻቸውን ጠየቅናቸው። 12 ሰዎቻቸውንና የሥራ መሪዎቻቸውንም በየስማቸው ጽፈን ወደ አንተ እንልክ ዘንድ መረመርናቸው፤ አለቆቻችውንም ጠየቅናቸው። 13 እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱልን፦ ‘እኛስ ምድርንና ሰማይን የፈጠረ የእግዚአብሔር ባሮች ነን።’ 14 ይህ ቤት ከብዙ ዘመን አስቀድሞ በታላቁና በብርቱው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ተሠርቶ ተፈጽሞ ነበር። 15 ነገር ግን አባቶቻችን ኀጢአት ሠርተው ሰማያዊውን የእስራኤል ፈጣሪ አሳዝነውታልና በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆርና በፋርስ ንጉሥ እጅ ጣላቸው። 16 ይህንም ቤት አፈረሰ፤ በእሳትም አቃጠለ፤ ሕዝቡንም ማረከ፤ ወደ ባቢሎንም ወሰዳቸው። 17 ቂሮስም በባቢሎን በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን ቤት ይሠሩ ዘንድ ጻፈ። 18 ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው ቤተ መቅደስ ያወጣውን፥ ባዳራሹም ያኖረውን የወርቅና የብር ንዋየ ቅድሳቱን፥ ንጉሥ ቂሮስ በባቢሎን ካለ አዳራሹ አውጥቶ ለዘሩባቤልና ለገዥው ለሰናባሶርስ ሰጣቸው። 19 ይህንም ንዋየ ቅድሳት ወስደው በኢየሩሳሌም ባለ ቤተ መቅደስ ያኖሩት ዘንድ፥ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ በቦታው ይሠሩት ዘንድ አዘዛቸው። 20 ከዚህም በኋላ ያ ሰናባሳሮስ በደረሰ ጊዜ በኢየሩሳሌም ያለ የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ጀመረ፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠሩ ነበር፤ ነገር ግን አልጨረሱም። 21 አሁንም ጌታችን ንጉሥ ሆይ! በባቢሎን ያለ የንጉሡን የቂሮስን መንግሥት የታሪክ መጻሕፍት ገልጠህ መርምር። 22 ንጉሡ ቂሮስ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ እንደ ፈቀደ ብታገኝ፥ ጌታችን ንጉሥ ሆይ! አንተም ፈቅደህላቸው እንደ ሆነ ስለዚህ ነገር ላክልን።” የንጉሥ ቂሮስ ትእዛዝ መገኘት23 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዳርዮስ በባቢሎን የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ይፈልጉ ዘንድ አዘዘ፤ በሜዶን አውራጃ በጣኒስ-ባሪ ከተማ ውስጥ የታሪክ መጽሐፉን ባኖሩበት በአንድ ቦታ ተገኘ፤ እንዲህም ይላል፦ 24 “በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመተ መንግሥት በየዕለቱ በእሳት መሥዋዕት የሚሠዉበትን፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዘ። 25 ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን፤ ሥራውም በሦስት ወገን በጥርብ ድንጋይ፥ ባንዲት ወገንም በሀገሩ አዲስ የዝግባ እንጨት ይሁን፤ ወጭውንም ከንጉሡ ከቂሮስ ዕቃ ቤት ይሰጧቸው ዘንድ አዘዘ። 26 ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው ከቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰደውን የወርቁንና የብሩን የእግዚአብሔርን ቤት ንዋየ ቅድሳት በኢየሩሳሌም ወዳለው ቀድሞ ወደ ነበረበት ወደዚያ ቤት ይመልሱት ዘንድ አዘዘ።” ንጉሥ ዳርዮስ ሥራው እንዲቀጥል ማዘዙ27 የእግዚአብሔር ባሪያ የይሁዳ አለቃ ዘሩባቤልና በይሁዳ ያሉ ሽማግሌዎች የእግዚአብሔርን ቤት በቦታው ይሠሩት ዘንድ የሶርያና የፊንቂስ ገዥ ሲሳኒስና ሳትራቡዛኒስ፥ ከእነርሱም ጋራ ያሉ ጓደኞቻቸው የሶርያና የፊንቂስ ሹሞች ቦታቸውን ይተዉላቸው ዘንድ አዘዘ፤ 28 “እኔም የእግዚአብሔርን ቤት ሠርተው እስኪፈጽሙ ድረስ ከተማረኩበት የተመለሱ የአይሁድ ወገኖች ሁሉ አንድ ሁነው ተሰማርተው የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዝኋቸው። 29 ከቄሊ-ሶርያና ፊኒቂ ከሚገባው ግብር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ፍየሎችንና ላሞችን፥ በጎችንም እንደ ሥርዐቱ ለእነዚህ ሰዎችና ለአለቃው ለዘሩባቤልም ሰጥታችሁ ደስ አሰኙአቸው። 30 እንደዚሁም የሚያነዱትን እንጨት፥ ስንዴውን፥ ጨዉንና ወይኑን፥ ዘይቱንም፥ የዘወትሩንም ወጭ ገንዘብ ሁሉ፥ በየዓመቱም የሚያደርሳቸውን፥ በኢየሩሳሌም ያሉ ካህናቱ ያሏችሁን ያህል ስጧቸው፤ ግብሩንም ሳትከራከሩ እነርሱ የሚሏችሁን የሚበቃቸውን ስጧቸው። 31 ስለ ንጉሡና ስለ ልጆቹ ለልዑል እግዚአብሔር ቍርባኑን ያቀርቡ ዘንድ፥ ስለ ሕይወታቸውም ይጸልዩላቸው ዘንድ። 32 “በዚች ደብዳቤ እንደ ተጻፈ አልሠራም የሚል፥ የሚከራከራቸውም ቢኖር ከራሱ ቤት እንጨት አምጥተው በዚያ ይስቀሉት፤ ገንዘቡንም ይዝረፉት፤ ለንጉሡ ቤትም ይሁን። 33 ስለዚህም ስሙ በዚያ የተጠራ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ ይከለክሏቸው ዘንድ፥ ክፉ ሥራም ይሠሩ ዘንድ እጃቸውን የሚያነሡ ነገሥታትንና አሕዛብን ሁሉ ያጥፋቸው። 34 እኔ ዳርዮስ እንዲህ አድርገው ተግተው ይሠሩ ዘንድ አዘዝሁ።” |